እንደ ፈረንጆቹ የዘመን አቆጣጠር በ1975 ፍቅሩ ማሩ እናት አገራቸውን ለቀው በስዊዲን የስደተኝነትን ህይወት መምራት ጀምረዋል፡፡በስዊዲን ቆይታቸው በልብ ህክምና ስፔሻላይዝድ በማድረግ ዶክትሬታቸውን የሰሩት ፍቅሩ ረዘም ላሉ ዓመታት በስደተኝነት በተቀበለቻቸውና ባስተማረቻቸው ስዊዲን በሚገኘው ሁዲክቫል ሆስፒታል (Hudiksvall) በሞያቸው ሲያገለግሉና በአገሪቱ ዮኒቨርስቲዎች ሲያስተምሩ ቆይተዋል፡፡
ዶክተሩ ፍቅሩ ለስደት የዳረጋቸው ደርግ ከወደቀ ረዘም ያሉ ዓመታት በኋላ የትውልድ አገራቸውን በሞያቸው ለማገልገል በማሰብ ከስዊዲን ያገኙትን የገንዘብ ድጋፍ በመያዝ ጭምር ወደ ኢትዮጵያ ጠቅልለው የገቡት በ2010 ነበር፡፡
ፍቅሩ በአዲስ አበባ ከተማ ለአገሪቱ የመጀመሪያው የሆነውን የግል የልብ ህክምና ክሊኒክ በመክፈት አገልግሎት በመስጠት ለልብ ህክምና ወደ ውጪ አገራት ማምራት ግድ ይላቸው የነበሩ የአገራቸውን ልጆች ከተጨማሪ ወጪዎች ሲታደጉ ቆይተዋል፡፡
በ2013 ኢህአዴግ የአገር ውስጥ ገቢ ሚንስትሩን ጨምሮ ብዛት ያላቸውን የንግድ ሰዎች በቁጥጥር ስር ሲያውልም ዶክተር ፍቅሩ ‹‹ለልብ ህክምና የሚውሉ መሳሪያዎችን ከባለስልጣናት ጋር በመመሳጠርና ጉቦ በመስጠት በዝቅተኛ የግብር ዋጋ አስገብተዋል ››ተብለው ለእስር ተዳረጉ፡፡
አቃቤ ህግ በፍቅሩ ላይ በመጀመሪያ አቅርቦት የነበረው ክስ በግዜ ሂደት እየተቀናነሰ መምጣቱ ቢታወቅም ፍርድ ቤቱ በአራት አመት ከስምንት ወራት እስራት በየነባቸው፡፡
የ66 ዓመቱ የልብ ህክምና ዶክተር በፍርድ ቤቱ የተጣለባቸውን የእስር ቅጣት ያጠናቀቁ ቢሆንም እስካሁን ድረስ አመክሮው ታስቦላቸው ሊለቀቁ አለመቻላቸው ብዙዎችን በተለይም የዶክተሩን ቤተሰቦች አሳስቧል፡፡
በቅርቡ ዶክተሩ በሚገኙበት ወህኒ ቤት ራሳቸውን ስተው በመውደቃቸው ረዘም ያሉ ሳምንታትን በሆስፒታል ውስጥ ለማሳለፍ ተገደዋል፡፡ዶክተሩ የመተንፈሻ አካል ችግር ያለባቸው በመሆኑም የቀዶ ህክምና ማድረግ እንደሚገባቸው ተነግሯል፡፡
የዶክተሩ የመጀመሪያ ልጅ ኤሚ ማሩ የአባትዋን ፈለግ በመከተል በስዊዲን በቅርቡ በዶክትሬት ተመርቃለች፡፡አባትዋ ሊፈቱ እንደሚችሉ ተስፋ በማድረጓም በአዲስ አበባ ተገኝታ ነበር ፡፡ነገር ግን ዶክተሩ ራሳቸውን ስተው በሆስፒታል ያገኘቻቸው ከመሆኑም በላይ እስካሁን ድረስ ነጻነታቸውን አላገኙም፡፡
ኤሚ በአባትዋ ጤንነትና ያለመፈታት ግራ በተጋባ ስሜት ሆና ‹‹ለምን እንዳልለቀቁት ሊገባን አልቻለም ››ያለች ሲሆን የፍቅሩ ጠበቃ ሃንስ ባግነር በበኩሉ ጉዳዩን ለአለም አቀፉ ፍርድ ቤት ለማቅረብ ጊዜው አሁን መሆኑን አምኗል፡፡
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የልብ ስፔሻሊስት በወህኒ ቤት ለማጣት የተቃረበበችበት ታሪክ ይለወጥ ዘንድ እንጮሃለን፡፡
No comments:
Post a Comment