Tuesday, August 9, 2016

ምን እንደማንታገስ (Why We Can't Wait)

Alemayehu, የአመፅ አልባ ትግል ሰባኪው ሉተር ኪንግ ስለአመፅ የተናገረውን ጠቅሶ ሳይ ተርጉመው አሰኘኝ።

ሲተረጎም፣ "ዛሬ ማታ ከፊታችሁ ቆሞ አመፆችን ማውገዝ ብቻ ለኔ በቂ አይደለም። በተመሳሳይ፣ ነባራዊውን እና ልንታገሰው የማይገባውን የማኅበረሰባችንን ሁኔታ አለማውገዝ ኅሊና ቢስነት ይሆንብኛል። እነዚህ ሁኔታዎች ናቸው ግለሰቦችን የሚፈልጉትን ትኩረት ለማግኘት ወደአመፅ እንዲገቡ የሚያደርጓቸው። ስለሆነም፣ ዛሬ መናገር ያለብኝ አመፅ ሰሚ ያጡ ሰዎች ቋንቋ መሆኑን ነው" ~ ማርቲን ሉተር ኪንግ (ትንሹ)።

ግን በቂ አልነበረም፣ ምክንያቱም ሰሞኑን ከጓደኞቼ ጋር ስንወያይ ‘ጥድፊያ በዛ’ የሚል ሙግት ይገጥመኛል። ግን እውነት ጥድፊያ አለ? ቢያንስ ያለፉት 10 ዓመታት የተከፈሉት መስዋዕትነቶች በቂ አልነበሩም? በቆየን ቁጥር ነገሮች እየረገቡ ነው ወይስ እየከረሩ? የኛ ትዕግስት በእስር፣ በስደት፣ በኑሮ ዋጋ እየከፈሉ ላሉት ምናቸው ነው? ለነዚህ ጥያቄዎች ማርቲን ሉተር ኪንግ ‘Why We Can't Wait’ በሚል ርዕስ እስር ቤት ፀንሶ በወለደው መጽሐፉ ከጠቃቀሳቸው ውስጥ ጥቂት እንዋስ እና በራሳችን ቋንቋ እንተርጉመው…

“‹በጣም አንቻኮል› የሚሉት ወግ ጠባቂዎች እና ‹አሁኑኑ ወጥተን ጥርግርጉን እናውጣው› የሚሉት ጠርዘኞች እንደምድር ዋልታዎች የተራራቁ እንደሆነ ነው የሚነግሯችሁ፡፡ ግን የሚያመሳስላቸው ነገር አለ፤ ሁለቱም ምንም ውጤት አያመጡም፡፡ ምክንያቱም ነጻ ለመውጣት እያለቀሱ ላሉት ሁለቱም አይደርሱላቸውም፡፡”

“ጊዜ በራሱ ገለልተኛ ነው፤ ለጥፋትም ለልማትም ሊውል ይችላል፡፡ ከጊዜ ወደጊዜ ክፉ ዓላማ ያላቸው ሰዎች ጊዜን መልካም ዓላማ ካላቸው ሰዎች ይልቅ በአግባቡ እንደሚጠቀሙበት እየተሰማኝ ነው፡፡ በዚህ ትውልድ ንስሐ መግባት የሚኖርብን ለክፉዎቹ ሰዎች መጥፎ ቃላትና ተግባራት ብቻ ሳይሆን ለመልካሞቹ ሰዎችም አስቀያሚ ዝምታ ነው፡፡ የሰው ልጅ በመሻሻል ጎዳና ላይ መጓዙ የማይቀር ጉዳይ አይደለም፤ መሻሻል የሚመጣው ደከመኝ ሳይሉ በሚሠሩ፣ ለመሥራት እና ከእግዜር ጋር ለመተባበር በሚፈቅዱ ሰዎች ጥረት ነው፡፡ እንዲሁም፣ ካለብርቱ ጥረት፣ ጊዜ በራሱ ለማኅበራዊ ፍዛዜ ተባባሪ ነው፡፡ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ያለብን፣ ጊዜው አንድን መልካም ነገር ለማድረግ ሁሌም ምቹ መሆኑን በማወቅ ነው፡፡”

“በርሚንግሃም ውስጥ ለምናደርገው እንቅስቃሴ በሙሉ ‹መጥፎ ሰዐት› የሚለው አስተያየት እንደሙት መንፈስ እያሳደደን ነው፡፡ ይህንን የሚሉን ሰዎች ግን የዕቅዳችንን ዳራ አያውቁትም… ስለጊዜ ለመናገር ኔግሮዎች ከ100 ዓመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ እየተሰቃዩ መክረማቸውን ስለማያስተውሉ በጣም መሳለቂያ ጉዳይ ይሆናል፡፡”

No comments:

Post a Comment

የምጣዱ እያለ የእንቅቡን፤ የእርስ በርስ ግጭት እና የመንግስት ምላሽ

በያሬድ ሃይለማሪያም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አሁንም ግጭቶች መበራከታቸው እና መፈናቀል መቀጠሉ የአገራችንን ፖለቲካ አሳሳቢ እያደረገው እና አገሪቱንም ወደ ችግር ውስጥ እየከተታት ይመስላል። መንግስት ለችግሮቹ የሚሰ...