የተለያዩ የአለም ሃገራት ሀገራቸውን ወክለው በሪዮ ( በወንዝ ማለት ነው ) ኦሎምፒክ እየተሳተፉ ይገኛሉ ። የኢትዮጵያ መንግስትም ከዜና ዘገባው ውስጥ 85 ከመቶ በላይ የዜና ሽፋን ሰጥቶት እየዘገበው ይገኛል ። እስኪ ስለ ወርቅ ሜዳይ ከማውራታችን በፊት ሜዳዩ ላማን እና ለምን ስለሚለውን እንነጋገር ። አዲስ መስመር እና ስም አይከፈልበትምና ይህንን ጉዳይ ባአዲስ መስመር ብንጀምረውስ?!
ኢትዮጵያ ሀገራችን በሪዮ ኦሎምፒክ በሩጫ ፥ ጡቻ በሚመስል የውሃ ዋና እና ሌሎችም ስፖርቶች ፥ ከፊሎቹን በምፅዋት ( እንደ ዋናው ) ቀሪዎቹን በብቃት ተሳትፋ እየተወዳደረች ትገኛለች ። እሳት የላሱት ልጆቿ ፥ የኦሎምፒክ ክብረ ወሰኖችን እየሰበሩ ዛሬም እንደ ትናንቱ ሃገራቸውን እያስጠሯት ይገኛል ። በኤሊና ጥንቸል ተረት ያደጉትም ሌሎቹ ተኝተው የሚጠብቋቸው ይመስል የምድር ወገብን በሚያህል ቦርጫቸው ዋና ዋኝተው ይቺን ምስኪን ሃገራቸውን መሳቂያ እና መሳለቂያም ሲያደርጓት አይተናል ።
በዚህ ፅሁፍ ስለማይረቡት ሳይሆን ስለሚረቡት ኢትዮጵያዊያኖች ነውና መዳሰስ የምፈልገው ሃሳቤን በነሱ እና እነሱ ላይ ብቻ ሰብስቤ ልቀጥል!
የሚረቡት ኢትዮጵያዊያኖች ከላይ እንደጠቀስኩት የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት አድርገውናል ። ከነዚህም ውስጥ የመጀመሪያውን ወርቅ በማምጣት እና የኦሎምፒክ ክብረወሰንን በመስበር ተአምር የሰራችው አልማዝ አያና ናት ። በዘልማዝ ድል ደስ ብሎኛል ። ስለ አልማዝ ሳስብ ግን አዝናለሁ ። የማዝነው ደሞ አልማዝ ለፍታ ፥ ምናልባትም የእድሜ ዘመን ህልሟን አሳክታ ፥ ከሃገሮች መሃል በድሏ ቀና ብላ የሃገሯን ባንዲራ ስታይ ምን ይሰማት ይሆን ብዬ ስለማስብ ነው ። አልማዝ አኩርታናለች ፥ እሷ ግን በኛ ትኮራለች ወይ የሚለው ጥያቄ ጭንቅላቴን ሰላም ነሳው ። አልማዝ በተሰለፈችበት አሸንፋ ፥ በቆመችለት አላማ ከአለም አትሌቶች እኩል ሳይሆን የበላይ ሆና ሀገሯን አስጠርታለች ። ግን ግን ፥ የኔ ብላ የተዋደቀችላት ሃገር ፥ በአለም አደባባይ « የኢትዮጵያ ልጅ » የተባለችባት ያቺ የኛ ምድር የአልማዝ ወንድሞች መታረጃ መሆኗን ሳስብ ፥ አልማዝ አሳዘነችኝ!
ከአልማዝ የወርቅ ሜዳይ ባሻገር ፥ ከአልማዝ የ ኦሎምፒክ ክብረ ወሰን ወዲያ ፥ ወዲያ ማዶ ያለውን የአልማዝ ጓዳ ፥ የሃገሯን ጉድ እና ጉዳንጉድ ለአፋታ አስቤ ፥ አልማዝ ከባንዲራው መሃል ቀና ብላ ቆማ በዚያች ቅፅበት ምን ይሰማት ይሆን ? በገመድ ከሚሳበው እና ማንም የኔ ብሎ ከማይቀበለው ባንዲራ ፥ ህዝብ እስከተፋው ስርአት ድረስ በተከበበው ድሏ ውስጥ ያለውን ሰዋዊ ስቃይ ፥ ማንነታዊ ህመም ፥ ነባራዊ ቁስል እያሰብኩ ለአልማዝ ድል አዘንኩ ። በአልማዝ ፍልቅልቅ የድል ደስታ ውስጥ የተቀበረውን ክምር ሀዘን ፥ የህዝብ ስቃይ እና ሰቆቃ ፥ እያስታወስኩ ፥ «የአልማዝን ድል ለማን ?» እነማንን ሊወክል ብዬ ራሴን ጠየቅሁ። ታዋቂው ሊባኖሳዊ ጠሃፊ ጅብራን ካህሊል ጅብራን «Your joy is your sorrow unmasked » የሚለው አባባል አለው ። የአልማዝ ደስታም ሃዘኗ ነፃነት ሲያገኝ የወጣ ሳቅ መስሎ ተሰማኝ ።
ሀገር ብላ የምታስባት ሃገር፣ ሀገሯ ሳትሆን የሞት ጉድጓድ መሆኗን ፥ እርሷ በሪዮ ሃምሳ ሳንቲም የምታህል ወርቅ ነክሳ ፎቶ ስትነሳ ፥ ባንፃሩ ዘመዶቿ ጥርሳቸውን ነክሰው ለመብታቸው እየተዋደቁ እንደሆነ በእኩል ቅፅበት አሰብኩት !
ለዚህ ለዛሬ ማንነቷ መሰረት ፥ ለመቅኒዋ ደም ወተት ፥ ለጉልበቷ ጅማት አጓት ፥ ለወገቧ ጨጨብሳ በቂቤ ጨቅጭቀው « አልማዝ ኪያ» እያሉ ያሳደጓት እነዚያ ደግ ገበሬዎች በሚታረዱበት ፥ በሚገደሉበት ፥ በሚታሰሩበት እና በሚዋከቡበት ሰአት ያገኘችው ድል ነውና ፥ የአልማዝ የደስታዋ ጫፉ ፥ የክብረ ወሰኗ ከፈፉ ፥ በሳቅ የተሸፈነ ለቅሶ ፥ በእልልታ የተለወሰ ኡኡታ የሆነ እንደሆነ ሆኖ ተሰማኝ ። አልማዝን ሆኖ ድል ማድረግ ሳይሆን የሚከብደው ፥ የድሉን በረከት ሃገርነቱን ለተወ ሀገር ሀገሬ ብሎ ይዞ መሄድ እንጂ ። የወርቅ ሜዳይ አጥልቆ ፥ በአለም አደባባይ የኢትዮጵያ ልጅ ተብሎ ፥ ተወድሶ እና ተሞግሶ ፥ ሬሳ የወጣበት ቤት አዲስ ሙሽራ ሆኖ መግባት እንዴት ያለ ስሜት ይሆን የሚፈጥረው ? የአልማዝ ድል ከደስታው ይልቅ ሃዘኑ ይበረታል ። አልማዝ ወንድም እህቶቿ ለማንነት ፥ ለክብር ፥ ለህልውና ሜዳይ እየተዋደቁ ባለበት ሰአት ፥ የአልማዝ ሜዳይ ከቁራጭ ወርቅነት ያለፈ ትርጉም ይኖረዋል ለማለት ይከብዳል ። አልማዝ ሩጣ ስታሸንፍ ፥ ሀገሯ ላይ ቁማ ግን ተሸንፋለች! ኑራ ተሸንፋለች ። ሰው ልሁን ብላ ሰውነቷን ተነጥቃ ተሸንፋለች ። አልማዝ አልማዝነቷ ተክዶ እንደ ትቢያ በየ ትቦው ላይ በጥይት ተገድላለች ። አልማዝ ወርቅ ይዛ ብትመጣም ፥ በወገኖቿ ስቃይ ምክንያት ወርቋ የነሃስ ያህል አያበራም ። ደስታዋ ከቅፅበት ድል ባሻገር ፥ በተነጠቀችው ሀገር ላይ የተጎሰመ ነጋሪት ነውና ፥ ድሏ ከአስጋሪነት ያለፈ ክብር የለውም ! ስለዚህ አልማዝ ታሳዝነኛለች!
ለማጠቃለል ያህል
የኛ ሜዳይ በህዝቦች ትብብር የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ የሚያመጣው ህዝባዊ ድል ነው ። የኛ ኦሎምፒክ ከተናቅንበት እና ከተረገጥንበት ቀና ብለን ሰው መሆናችንን የምናሳይበት ቀን እስኪመጣ ድረስ የምናደርገው ትግል ነው ። የኛ ወርቅ ላንገታች ሳይሆን ለህሊናችን እረፍት የሚሰጠን የሰው ልጆችን ክብር በአግባቡ ለመመለስ እና ለማስመለስ የምናደርገው ትግል እና ትንቅንቅ ነው ። በዚህ ( በህዝባዊ ትግሉ ማለቴ ነው ) ኦሎምፒክ ውስጥ ያላችሁ ሁሉ ስለዛኛው ( ስለ ጠገራው ኦሎፒክ ) በማሰብ ጊዜያችሁን አታጥፉ። ያለ ሀገር የሀገር ድል ሊኖር አይችልምና!
ኄኖክ የሺጥ
No comments:
Post a Comment