Thursday, November 27, 2014

በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የተከሰሱት እነ አብርሃ ደስታ ለታህሳስ 9 ቀጠሮ ተሰጠባቸው::

#‎Ethiopia‬





የሽብር ክስ የቀረበባቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ለታህሳስ 9 ቀጠሮ ተሰጠባቸው

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር

በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው አራቱ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች እና በተመሳሳይ መዝገብ የተከሰሱት ሌሎች ስድስት ተከሳሾች የቀረበባቸውን የክስ መቃወሚያ እንዲያቀርቡ ለታህሳስ 9 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡


የአንድነት፣ የሰማያዊና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች የሆኑት አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ እና ዳንኤል ሺበሽ በሚገኙበት የክስ መዝገብ የተከሰሱት አስሩም ተከሳሾች ዛሬ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት፣ የተከሳሽ ጠበቆች በጠየቁት መሰረት የተከሳሾቹን የክስ መቃወሚያ ለመቀበል ፍርድ ቤቱ ለታህሳስ 9/2007 ዓ.ም ጠዋት 3፡00 ቀጠሮ ይዟል፡፡

በሌላ በኩል የተከሳሽ ጠበቆች በተከሳሾች ላይ አቃቤ ህግ አለኝ ያላቸውን የሰነድ ማስረጃዎች ዝርዝር እንዲደርሳቸው መጠየቃቸው የሚታወስ ሲሆን፣ አቃቤ ህግ ግን እስካሁን ድረስ ዝርዝሩን ለተከሳሽ ጠበቆች አለማቅረቡን በመጥቀስ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲደርሳቸው እንደሚያደርግ አስረድቷል፡፡ የማስረጃው አለመሟላት ሁሉንም ተከሳሾች የሚመለከት አለመሆኑን ያወሳው አቃቤ ህግ፣ ለአብነት 10ኛ ተከሳሽ አቶ ተስፋዬ ተፈሪ ከብሄራዊ መረጃ ደህንነት የተገኙ ማስረጃዎች እንደማይመለከቱት አስረድቷል፡፡

ተከሳሾቹ በ1994 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ እና አወዛጋቢውን የፀረ-ሽብር አዋጅ አንቀጾች በመተላለፍ በሽብር ወንጀል ተካፍለዋል፣ ድርጊቱን ለመፈጸም ተንቀሳቅሰዋል፣ ህዝብን ለአመጽ ቀስቅሰዋል በሚል ተጠርጥረው ጥቅምት 21 ቀን 2007 ዓ.ም በይፋ ክስ እንደተመሰረተባቸው የሚታወስ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment

የምጣዱ እያለ የእንቅቡን፤ የእርስ በርስ ግጭት እና የመንግስት ምላሽ

በያሬድ ሃይለማሪያም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አሁንም ግጭቶች መበራከታቸው እና መፈናቀል መቀጠሉ የአገራችንን ፖለቲካ አሳሳቢ እያደረገው እና አገሪቱንም ወደ ችግር ውስጥ እየከተታት ይመስላል። መንግስት ለችግሮቹ የሚሰ...