Thursday, September 4, 2014

ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል (ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም)



ጉልበት አራዊት የሚተዳደሩበት ሕግ ነው፤ ሕገ አራዊት የሚባለው አራዊት የሚተዳደሩበት ጉልበት ነው፤ በአራዊት ዓለም ማናቸውም ነገር በጉልበት ያልቃል፤ በሰዎችም መሀከል ጉልበት አድራጊ-ፈጣሪ ሆኖ ጎልቶ ሲወጣ የአእምሮንና የኅሊናን መዳከም ወይም ጭራሹኑ አለመኖር ያመለክታል፤ ጉልበት አለን በማለት፣ ወይም ተመችቶናል በማለት፣ ወይም ጠያቂ የለብንም በማለት የማንኛውንም ሰው ሰብአዊ መብቱንና ሰብአዊ ክብሩን መግፈፍ ሦስት ነገሮችን ያመለክታል፤ አንደኛ ጉልበት እንጂ አእምሮና ኅሊና እንደሌለ፣ ሁለተኛ ጉልበት እንጂ ሕግ እንደማይከበር፣ ሦስተኛ በአንተ ላይ እንዲያደርጉብህ የማትፈልገውን አንተም በሰዎች ላይ አታድርግ የሚለውን ሕግ መጣስን ያሳያል፤ በመጨረሻም፣ ዘግይቶም ቢሆን በራስ ላይ ቅሌትን መጋበዝን ያስከትላል፤ የሌላውን ሰውነት ስናረክስ ሰውነትን በጠቅላላው ማርከሳችን ነው፤ ሰውነትን በጠቅላላው ስናረክስ ራሳችንን ከነጉልበታችን ማርከሳችን ነው፤ ራሳችንን፣ ሰውነታችንን ካረከስን በኋላ ዋጋ የለንም፤ ለራሳችን ዋጋ ከሌለን ለሌለች ሰዎችም ዋጋ አንሰጥም፤ ያኔ ክፉ በሽታ ይይዘናል፤ እግራችን ስር በወደቀ ሰው ስቃይ የምንደሰትና የምንስቅ፣ የምንፈነድቅ እንሆናለን፤ ያን ጊዜ የለየለት በሽተኛ ሆነናል።


ይሄ በሽታ ያቃዣል፤ ከሰው ሁሉ በላይ ያሉ ያስመስላል፤ አግሩ ስር የወደቀው አንድ ሰው የሰው ልጅ በሙሉ ይመስለዋል፤ በሽተኛነቱን ስለማያውቅ በሽታው ከሰው በላይ ያደረገው ይመስለዋል፤ እንዲህ ዓይነቱ በሽተኛ በሕግ አሰከባሪነት ሥራ ውስጥ ሲገባ ሕግ የአንድ ማኅበረሰብ ትምክህትና መከታ በመሆን ፋንታ የበሽተኞች በትር ይሆናል፤ በደርግ ዘመን የአራት ኪሎው ግርማ የሠራውን እናውቃለን፤ ዛሬ ደግሞ ልዩ ግርማዎች አሉ፤ መልካቸውን ከካሜራው ጀርባ ደብቀው በሰው ስቃይና አበሳ በሳቅ እየተንከተከቱ ጀብዱዋቸውን በቴሌቪዥን የሚደረድሩ ጀግኖች መጥተዋል፤ መሣሪያ ይዞ መሣሪያ ባልያዘ ሰው ላይ ጀግና መስሎ ለመታየት የሚሠራው ጨዋታ ራስን ክፉኛ ከማጋለጥ በቀር ሌላ ፋይዳ የለውም።


በኢትዮጵያዊ ሰውነት ላይ ማናቸውንም ከሕግና ከሰብአዊነት ውጭ የሆነ ሙከራ ለማድረግ የውጭ አገር ሰዎች ዕድሉን ይፈልጉት ይሆናል፤ ለነሱ ሰዎች ስላልሆን ሰብአዊነት አይሰማቸውም፤ ከአገራቸው ሕግም ውጭ በመሆናቸው በሕግ አይገዙም፤ ዋናው ውጤት ግን ለኢትዮጵያ ሕግ አስከባሪዎች የሚያስተምሩት ግዴለሽነት ነው፤ መታሰር በብዙ ምክንያቶች ይመጣል፤ ስለዚህ በሠለጠነው ዓለም የተለያዩ እስረኞች በተለያየ ሁኔታ ይጠበቃሉ፤ አንዳንዶቹ እንዲያውም በቤታቸው ውስጥ እየተጠበቁ ይቆያሉ፤ ኢትዮጵያ በራስዋ ሥልጣኔ በምትተዳደርበት ዘመን መሳፍንትና መኳንንት የሚታሰሩት በወርቅ ወይም በብር ሰንሰለት ነበር፤ ግዞትም፣ የቁም እስርም ነበር፤ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ እስረኞች ሁሉ እኩል ናቸው፤ በቃሊቲ ለየት ያለ አያያዝ የሚታየው ለሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ብቻ ነው።


ጉልበትን በጉልበት እቋቋማለሁ የሚል ሰው ሲሸነፍ አያስደንቅም፤ አዲስም አይደለም፤ በአለፉት አርባ ዓመታት እየተሸነፉ ከትግሉ ሜዳ ወጥተው በተለያዩ የምዕራባውያን አገሮች የሙጢኝ ብለው የተቀመጡ አሉ፤ በተባበሩት መንግሥታት ደንብ የሙጢኝ ማለት መብት ነው፤ ይህንን መብት መጣስ የመንግሥተ ሰማያትን በር መድፈር ነው፤ በጎንደር የአደባባይ ኢየሱስን ቤተ ክርስቲያን በር መድፈር ነው፤ በአዲስ አበባ የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን በር መድፈር ነው፤ በአዲስ አበባ የአንዋር መስጊድን በር መድፈር ነው፤ ወደመሬት ስንወርድም የሙጢኝ የተባለው አገርን መንግሥት መድፈር ነው፤ የተባበሩት መንግሥታት ደንብን መጣስ ነው፤ ለነገሩ የመንግሥተ ሰማያትን በር መድፈር ከተቻለ ሌላው ምን ያቅታል!


የሙጢኝ ያለን ሰው በአፈና መያዝና ወደአገር ማስገባት አንድ ችግር ነው፤ ይህ የጉልበተኛነት መገለጫው ነው፤ ሁለተኛው ችግር የተያዘው ሰው መብቱና ክብሩ ሳይጓደልበት ማስረጃዎችን ሰብስቦ ለነጻ ፍርድ ቤት አለማቅረቡ ነው፤ በቴሌቪዥን እንደታየው አካላዊ ጉዳት እንደደረሰበት ባይታወቅም፣ ጥልቅ መንፈሳዊ ጉዳት እንደደረሰበት ይታያል፤ በብዙ አገሮች ሕጎች አንድ ሰው ራሱን እንዲወነጅል አይገደድም፤ ሕጋዊ ምርመራም በቴሌቪዥን በአደባባይ አይካሄድም።


ስለዚህም በተጠርጣሪው ላይ የተደረገው ሁሉ ሕጋዊ አይደለም፤ በነጻ ፍርድ ቤት ቢቀርብም በቴሌቪዥን የተናገረው ሁሉ ቢያስታውሰውም በማስረጃነት የሚያገለግል አይመስለኝም፤ ስለዚህም ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል።


ከአፍሪካ አህጉር ወጥቶ የቀይ ባሕርን አቋርጦ አንድ ሰው፣ ገና ወደፊት ክፉ ሊሠራ ይችላል በሚል ሂሳብ በጉልበት አፍኖ ማምጣት የብዙ ነፍሶች ዕዳን ተሸክመው በኢጣልያ ኤምባሲ የሙጢኝ ብለው ተደላድለው የተቀመጡትን የደርግ አባሎች ማስታወስ ግዴታ ይሆናል፤ አድርጋችኋል የተባሉትን ሰዎች የሙጢኝ የማለት መብት አክብሮ አስበሃል የተባለውን ሰው የሙጢኝ የማለት መብት መጣስ ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል።


ከፖሊቲካና ከምናምኑ፣ ጉልበተኛነትንም ከማረጋገጡ በላይ ሌላ ትልቅ ነገር አለ፤ አገር የሚባል ነገር አለ፤ ይህ በአንድ ግለሰብ ላይ የተገኘ ጊዜያዊ ድል የአገርን ከብር የሚያጎድፍና የሚያቀል ይሆናል፤ የአንድ አገርን የመንግሥት ሥልጣን የያዘ አካል አንድ ግለሰብን በአደባባይ ከሕግ ውጭ ለማጥቃት ሲሞክር የራሱን ክብር ዝቅ ያደረግበታል፤ ስለዚህም ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል።


በእኔ ዕድሜ ሰው በአደባባይ ሲገረፍ አይቻለሁ፤ ሰው ተሰቅሎ አይቻለሁ፤ የዚያን ዘመን የእውቀት ደረጃ የዚያን ዘመን የሰው ልጆች የመንፈስ እድገት ደረጃ ያመለክታል፤ የእውቀትም የመንፈስም ደረጃ በጣም ዝቅተኛ ነበረ ማለት ነው፤ ስለዚህም ይህንን ያደረጉትን ዛሬ አንወቅሳቸውም ይሆናል፤ የታሪካችን ጉድፍ መሆኑን ግን ልንፍቀው አንችልም፤ ስለዚህም ሌላ ጉድፍ እየጨመርንበት ታሪካችንን ማቆሸሹ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ይበልጣል።


ቅጣት በሕግና በሥርዓት ይደረግ ማለት ያጠፋ ሰው አይቀጣ ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ምንም አቅም የሌለውን ሰው ይዞ በአደባባይ ማሰቃየትና ማዋረድ አገርንና ሕዝብን ማዋረድ ነው፤ የሰብአዊነትንም የሕጋዊነትንም ሚዛኖች ይሰባብራል።


ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም

ሐምሌ 2006

(ምንጭ: Mesfin Wolde-Mariam Blog)

No comments:

Post a Comment

የምጣዱ እያለ የእንቅቡን፤ የእርስ በርስ ግጭት እና የመንግስት ምላሽ

በያሬድ ሃይለማሪያም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አሁንም ግጭቶች መበራከታቸው እና መፈናቀል መቀጠሉ የአገራችንን ፖለቲካ አሳሳቢ እያደረገው እና አገሪቱንም ወደ ችግር ውስጥ እየከተታት ይመስላል። መንግስት ለችግሮቹ የሚሰ...