Saturday, November 28, 2015

ዋናው ጥያቄ ከሚመቸው አልጋ ወይስ ከማይመቸው መንገድ የቱን ትመርጣለህ? የሚለው ነው።


ብዙዎቻችን በሚመቸው ክልል (comfort zone) ውስጥ ሆነን መስጠት የሚገባንን ሳንሰጥ ማበርከት የሚገባንን ሳናበረክት ማለት ያለብንን ሳንል መስራት ያለብንን ሳንሰራ እናልፋለን።የበለጠ አሳዛኝ የሚያደርገው ደሞ ማድረግ፣መስጠት፣ማበርከትና መስራት ያልቻልነው ስለማንችል ሳይሆን የምንችል ስላልመሰለንና ከሚመቸው ክልላችን መውጣት ስላቃተን ነው። በእርግጥ ከሚመቸው ክልላችን ወቶ ውጪ የማይመቸው ጎዳና ላይ መሮጥ አስቸጋሪ ነው። ግን መራመድ ካልተጀመረ እንዴት መሮጥን ማሰብ ይቻላል? መሮጥ ካልተጀመረ እንዴት የመጨረሻዋ ማሸነፊያ መስመር ጋ ይደረሳል? የመጨረሻዋ መስመር ጋ ካልተደረሰ እንዴት እራስን ለሌላ ድልና ለተሻለ አላማ ማዘጋጀት ይቻላል?
ሁሉም የሚሆነው እራስን በሚመቸው አልጋ ላይ አስተኝቶ እረፍት እያደረጉ ሳይሆን በማይመቸውና በሚጎረብጠው መንገድ በሚቀዘቅዘው አየር በከካዱ በሚነፍሰው አየርና በምታቃጥለው ጸሀይ ውስጥ ማለፍ ሲቻል ነው።
"የሚመቸው አልጋ ውስጥ ያለው እንቅልፍ ብቻ ነው" እንቅልፍ ውስጥ ደሞ ህልም ብቻ ነው ያለው። ህልም ውስጥ ደሞ ያሉት የማይጨበጡና የማይዳሰሱ ምናቦች ብቻ ናቸው። የሚመቸው አልጋህ (ምቹ ክልል comfort zone) ላይ ረጅም ጊዜ ማሳለፍህ ከምቾት ያለፈ ምንም ለውጥ ይዞልህ አይመጣም። ውስጣዊ እርካታንም አይሰጥህም።
ዛሬ የሚመቸውና የማይኮሶኩሰው አልጋህ ላይ ከሆንክ ያለምንም ማንገራገር ብድግ ብለህ ተነስና እኔ የማይመቸውንና የማይደላውን ረጅሙን ጎዳና እመርጣለሁ በል። በማይመቸው ውስጥ ሌሎች ብዙ የሚመቹ አሉና። አሁን ያለንበት የመጨረሻው የምቾት ጣሪያ ቢመስለንም ከዚ የበለጡ ብዙ ምቾቶችና የተሻሉ እድሎች አሉ። እራሳችንን ለጊዜው በሚመቹ ነገሮች ከበን የሩቁን የምቾት ጥግ አላየነውም እንጂ።
እኔ የታላቁ ሩጫ ላይ ስሮጥ የምሮጥበት መሬት ከምተኛበት አልጋ ብዙ እጥፍ እንደሚቆሮቁርና የአካባቢው አየር ንብረትም ጠባቧ ክፍሌ ውስጥ ካለው የተመጣጠነ አየር እንደሚለይና እንደማይመቸኝ አውቄዋለሁ። በተጨማሪም በተዘጋው ክፍሌ ውስጥ አግኝታኝ የማታውቀው ጸሀይዋ እንደፈለገች እንደምታገኘኝም ተረድቻለሁ። ግን ይህንን ሁሉ ባውቅም አልጋዬ ላይ ያለውን ድሎት መሬቱ ላይ ላገኘው እንደማልችል ብገነዘብም ለመሮጥ ወሰንኩ!
ከሚሞቀው አልጋዬ ወጥቼ በማይመቸው ጎዳና ላይ በመሮጤ ከብዙ ሰዎች ጋ ተገናኘሁ። ለቀጣይ የተሻሉ ስራዎችን የምሰራበት እድሎችን የሚያመቻቹልኝ በሮች ተከፈቱልኝ። ከነ ጥሩነሽ ከነ ገንዘቤ ከነ ስለሺ ከነ ገብረ እግዚአብሔር ከነ ቻቺ ከነ ጋሽ አበራ ሞላ ከነ እከ የመሳሰሉ ምርጥ ሰዎችን ለማግኘት ቻልኩ። ከሁሉም በላይ የሀይሌ ገ/ስላሴ የመጨረሻው ሩጫ ላይ መሳተፌ ከምንም በላይ ደስታን በውስጤ ሞላው። የሮጥኩት 115 ሜትርም ከሀገር ውስጥ አልፎ በሱፐር ስፖርትና በእንግሊዙ ቻናል 4 ላይ በቅርቡ ይታያሉ። በተጨማሪም ከብዙ አድናቂዎቼ ጋ ተገናኘሁ። እስኪ አስቡት እኔ ራሴን "እኔ ምንም የማልረባ የአልጋ ቁራኛ ነኝ" ብዬ ደምድሜ በሚመቸው አልጋዬ ላይ ተጋድሜ ቢሆንስ ኖሮ፤እኔንና ሱፐር ስፖርትንና ቻናል 4 በተጨማሪም የሀገር ውስጥ ስፖርት ጋዜጠኞች እንደ ፍሰሀ ሳምራዊትና ንዋይን ከመሳሰሉ ጎበዝ ጋዜጠኞች ጋ በምን ክንያት እገናኝ ነበር? ምንስ አንድ ሊያደርገን ይችል ነበር?
አያችሁ በሚመቸው አልጋ ውስጥ ራሴን ብደብቅ ኖሮ እነዚህ ሁሉ ሰዎች በሂወቴ ውስጥ አይገቡም ነበር። ከምንም በላይ ሩጫውን በመሮጥ ለራሴ ብርታትን አስተማርኩት፣ከመተኛት ምንም እንደማይገኝ አወኩ፣ከምቾት ይልቅ ስኬት በህመም ውስጥ ተደብቃ እንደምትገኝ አረጋገጥኩ፣ከምቾት ይልቅ በስቃይ ውስጥ ሲታለፍ መጨረሻዋን መስመር ማለፍ እንደምችል አየሁ!
ምናልባት በጣም ቀስ ብዬ ይሆናል የሮጥኩት፤ብቻ ሮጫለሁ።
ምናልባት ከታሰበው ጊዜ በታች ይሆናል የገባሁት፤ብቻ ሮጫለሁ።
ምናልባት ስሮጥ ምንም ምቾት አልተሰማኝ ይሆናል፤ብቻ ምንም ሳላቆም ሮጫለሁ።
ምናልባት ከጓደኞቼ ጋ ተጋፍቼ መሮጥ ስለማልችል ብቻዬን ሮጬ ይሆናል፤ብቻ ሮጫለሁ።
አሁን እግዚአብሔር ይመስገን የኡሴም ቦልት ሪኮርድን ልሰብረው 3 ደቂቃ ከ11 ሰከንድ ብቻ ነው የቀረኝ።
አሁን አንተም ከሚመቸው አልጋህ ላይ ተስፈንጥረህ ተነስና ራስህን በማይመቸው ጎዳና ውስጥ ከተህ የሚመቸውን የተሻለ ጎዳና ጥረግ። ከሚሞቀው አልጋህ ውስጥ ውጣና በቀዝቃዛው አየር ውስጥ አንተነትህን ፈልገው። የከበሩ ድንጋዮች ከተራሮች ንብርብር ስር ተደብቀው እንደሚገኙ እንጂ ከሚሞቀው አልጋችን ስር በቀላሉ እንደማናገኝ ሁሉ የምንፈልገውን የምንመኘውንና የምናልመውንም በሚመቸው አልጋችን ውስጥ ተቀብረን ልናገኘው አንችልም።
የሚቀጥለውን አብረን እንበል
እኔ....... .......... ..........(በባዶ ቦታው ስምህን ወይም ስምሽን አስገቡ) የማሸነፊያዋን ቀን በጉጉት እየጠበኩ ቁጭ የምል ሳይሆን በየቀኑ ያለማቋረጥ ልምምድ የምሰራ "አትሌት" ነኝ።
እኔ.......... ......... ...........በማይመቸው አየር ንብረት ሮጬ በማይመቸው መንገድ ሮጬ የሚመቸውን ህይወቴን የማስተካክል አትሌት ነኝ።
እኔ......... .......... ............የመጨረሻዋን መስመር በጉጉት እየጠበኩ አሁን የሚገጥመኝን ህመም ከቁብ ሳልቆጥር ሩጫዬን የምቀጥል ጎበዝ አትሌት ነኝ።
እኔ.......... .......... ..........መሰናክሎችን ሁሉ እያለፍኩ አንደኛ የምወጣ አትሌት ነኝ።
እኔ አትሌት ........... .............. ..............ነኝ።
ሰአሊ(አትሌት) ብሩክ የሺጥላ

No comments:

Post a Comment

የምጣዱ እያለ የእንቅቡን፤ የእርስ በርስ ግጭት እና የመንግስት ምላሽ

በያሬድ ሃይለማሪያም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አሁንም ግጭቶች መበራከታቸው እና መፈናቀል መቀጠሉ የአገራችንን ፖለቲካ አሳሳቢ እያደረገው እና አገሪቱንም ወደ ችግር ውስጥ እየከተታት ይመስላል። መንግስት ለችግሮቹ የሚሰ...