እኔ የምሰራበትን ቦታ ለመድረስ እንደሚከተለው አድርጉ፡፡ በመጀመሪያ ኢህዴግ ከገባ ወዲህ ነጭ ጤፍ ተፈጭቶበት የማያውቀው ወፍጮ ቤት እለፉ፡፡ በመቀጠል ኢህአዴግ ከገባ ወዲህ ተቃዋሚ አሸንፎበት የማያውቀውን የምርጫ ቦርድ ተሻገሩ፡፡በመቀጠል ተሻለ ድራፍት ቤት ላይ ቁሙ፡፡እሱ የእኔ የስራ ቦታ ነው፡፡
ብርጭቆ እያጠብኩ በመስኮቱ አሻግሬ አያለሁ፡፡አይነ ስውሩ ደንበኛየ ይታየው ከሩቁ ይታየኛል፡፡ይታየው ቆፋሮ በበዛበት መንገድ ላይ እየተወላከፈ ሲያዘግም ይታየኛል፡፡ ይታየው እንደ ተለመደው ቻይናዊያንን በለሆሳስ እየተሳደበ ይሆናል፤ ‹‹እኝህ የሰው ጃርቶች ደህናውን መንገድ ቆፍረው ቆፍረው ክንፍ አስመኙን እኮ ጎበዝ፡፡››
የ ድራፍት ቤቱን በር ገፍቶ ከመግባቱ በፊት ወደ ምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት ዞር አለና የተለመደውን ሀረግ አስወነጨፈ፤‹‹እንደምን አመሻችሁ ሙታን!››
በጽ/ቤቱ ውስጥ ያሉ ሁሉ ሰራተኞች እየተቀባበሉ ሲረግሙትና ሲዝቶበት ከሩቁ ተሰማኝ፡፡
‹‹አንተ ሰውዬ …ኧረ ተወን…ኧረ ተወን››
‹‹ከግንቦት ሰባት በሚደረግልህ ድጋፍ የምትጣጣ መሆኑን ያጣነው እንዳይመስልህ፡፡››
‹‹ ቸሩ መድሃኒዓለም አለ እንደሆን አንተንም እንደ አንድነት ፓርቲ ብትንትን ያድርግህ!››
ሳይመልስላቸው ወደ ውስጥ ዘለቀና ጥግ ላይ ባለች ቦታው ተቀመጠ፡፡ትዕዛዙን ሳልጠብቅ የገብስ አረፋ የሚደፍቅ ብርጭቆ ጠረጴዛው ላይ አስቀመጥኩለት፡፡በትሩን እያጣጠፈ ፤‹‹አንበሳው! ስለ ግንቦት ሰባት የሰማኸው አዲስ ነገር አለ?›› አለኝ፡፡
‹‹አልሰማሁም ጋሽ ይታየው፡፡››
‹‹ዛሬም ኤርትራ ውስጥ ናቸው?››
‹‹ቢሆኑ ነው እንጂ አዲስ አበባ ቢገቡማ በዚህ በኩል ሲያልፉ ይታየኝ ነበር፡፡››
ጭንቅላቱን በሃዘኔታ ነቀነቀ፡፡
‹‹እስከ ግንቦት 20 የሚደርሱ አይመስልህም?›››
‹‹አይመስለኝም ጋሽ ይታየው፡፡››
‹‹ አይ አለመታደል ፡፡ለሃያ አራተኛ ጊዜ እንዳያልፉት የለምን ልንሰማ ነዋ! ››
በቅርቡ በምርጫ ቦርድ ድማሚቲ የተበታተነው ፓርቲ አባል የሆነው ዘሪሁን አንገቱን ደፍቶ ወደ ድራፍት ቤቱ ሲዘልቅ ታየኝ፡፡ጋሽ ይታየውን ከነድራፍቱ ትቸው ለመታዘዝ ወደሱ አቀናሁ፡፡
ቀና ብሎ ሳያየኝ፤‹‹ጠንከር ያለ መጠጥ አምጣልኝ! አለኝ››
‹‹ጋሽ ዘሪሁን በዚህ ሰዓት ጠንከር ማለት እንጂ ጠንከር ያለ መጠጥ ምን ያደርግለሃል፡፡መበተን በናንተ አልተጀመረ፡፡የዘንድሮ ምርጫ ቦርድ እንኳን ፓርቲን የቆየ ትዳርን ከማፍረስ ወደኃላ እንደማይል የታወቀ ነው፡፡እባክህን ዛሬ ቀለል ያለ መጠጥ ጠጣ-እስቲ እሺ በለኝ›› ላጽናናው ሞከርኩ፡፡ጭንቅላቱን በተቃውሞውን ነቀነቀ፡፡
‹‹በፍጹም ይልቅ ምን ጠንከር ያለ መጠጥ አላችሁ?››
ጥረቴ እንዳልተሳካ ተሰማኝ፡፡
‹‹ውስኪ አለ!››
‹‹ከእሱ ጠንከር ያለ ነው የምፈልገው!››
‹‹ቮድካ አለ፡፡››
‹‹ከእሱ ጠንከር ያለ ነው የምፈልገው፡፡››
‹‹ጂን አለ፡፡››
‹‹ ከእነዚህ ጥንከር ያለና የሚጠጣ ነገር የላችሁም?››
‹‹እንግዲህ ከነዚህ ጠንከር የሚለው ሽጉጥ ነበር ለጊዜው ጨርሰናል፡፡››
ወደ ባንኮኒየ በማዘግምበት አፍታ ንብ የተሳለበት ቲሸርት የለበሰ ቦርጫም ሰውየ ፈገግታውን አስቀድሞ ወደ ድራፍት ቤቱ ዘለቀ፡፡ገና ከመግባቱ ወደ እኔ አቅጣጫ ሲንደረደር መጣና ማጅራቴን ይዞ ግንባሬን ሳመኝ፡፡ እኔን ለቀቀና እጆቹን በድል ዘይቤ ወደ ኮርኒሱ አስወንጭፎ ፤‹‹መጭው ዘመን ከኢህአዴግ ጋር ብሩህ ነው…››ብሎ ከመናገሩ የድራፍት ቤቱ መብራት ድርግም አለ፡፡
ሰውየው በዳበሳ ወንበር ፈልጎ ከጋሽ ይታየው ጎን ተቀመጠ፡፡መብራቱ የተመከረ ይመስል ይሄኔ ተመልሶ በራ፡፡የሰውየው ደስታ ተመለሰ፡፡
‹‹ወንድሜ ዛሬ ያንተ ወጪ በኔ ይሸፈናል፡፡ ያሻህን ጠጣ፡፡››አለና የጋሽ ይታየውን ትክሻ መታ መታ አደረገው፡፡
ጋሽ ይታየው ትን አለው ‹‹ማርያምን በልስቲ››
‹‹ምነው ተጠራጠርክ እንዴ?››
‹‹አይ…እንደሱ ማለቴ ሳይሆን…ደፈርከኝ ባትለኝ እናንተ የመንግስት ሰዎችን ማመን ይከብዳል፡፡ ከደቂቃ በፊት ያላችሁትን ከደቂቃ በኃላ ትሽራላችሁ፡፡ሌላው ይቅርና ባለፈው ‹ሞተ !ተቀበረ!› ያላችሁትን ጠቅላይሚኒስተር በቀደምለት ‹ተነሳ !አዲሱን ባቡር መረቀ !አላችሁን፡፡ ብጠራጠር አትፍረድብኝ፡፡‹ተጋብዘሃል!› ብለህ ስታበቃ ‹ ክፈል እና እና እንውጣ !›ብትለኝ ምን ይውጠኛል፡፡››
ሰውየው ያመጣሁለትን ድራፍት ሳይስፈቅድ ከጋሽ ይታየው ብርጭቆ ጋር አጋጭቶ በአንድ ትንፋሽ ጨለጠና ለሁለተኛው በጣቱ ጠራኝ፡፡ሁለተኛውን ብርጭቆ ይዤ ስጠጋው
‹‹ይገርምሃል በጣም ጠምቶኝ ነበር ፡፡››አለኝ
ፈንጠር ብሎ የተቀመጠው ጋሽ ዘሪሁን ቀና ብሎ አየው በልቡ ‹‹ከደደቢት በረሃ ነው እንዴ የመጣህ›› የሚለው ይመስላል፡፡፡ልስቅ አኮበኮብኩና የሰውየውን ግልምጫ ሳስተውል የዛሬውን ሳቅ በይደር አቆይቸው ወደ ቦታየ ተመለስኩ፡፡
‹‹ለመሆኑ ይሄ ሁሉ ፈንጠዝያ ለምኑ ነው፡፡›› አለ ጋሽ ይታየው የመጋበዝ ጉዳዩ እንዳይረሳሳ በማሰብ
‹‹ቴሌቭዥን አትከታተልም እንዴ?››
‹‹ብዙ ጊዜ አልከታተልም፡፡››
‹‹ለምን?››
‹‹አማካይ የመኖሪያ ዕድሜየን ከፍ ላድርግ ብሎ ነዋ፡፡›› አልኩ በልቤ፡፡ሰውየው ሁለተኛውን ብርጭቆ አጋመሰና እንደ አንበሳ አገሳ፡፡
‹‹ጮማ ጮማ ወሬ አምልጦኃላ፡፡ምርጫው ሳይጀመር ብዙ ፓርቲዎች በበቃኝ መውጣታቸውን አልሰማህማ፡፡›› ሰውየው ወደ ዘሪሁን አቅጣጫ የጎሪጥ አየ፤ ዘሪሁን ባዶው ጠረጴዛ ላይ እንዳረቀረ ነው ዝም ብሎ ያስባል፡፡ጋሽ ይታየው አነጋገሩን ለመደገፍም ለመቃወምም መቸገሩን የማያዩ አይኖቹን የጋረደበትን መነጠር ሽቅብ በመግፋትና የድራፍቱን ብርጭቆ በእጁ መካከል በማፍተልተል አሳየ፡፡ ‹‹ለምን ውስኪ አልጋብዝህም! ወስኪ ጠጣ ባክህ!›› አለ ሰውየው፡፡
‹‹ማርያምን በል እስቲ!››
‹‹ሙት ስልህ….መጭው ጊዜ ከኢ-››
መፈክሩን ከመጨረሱ በፊት የወስኪ ጠርሙስ እና ብርጭቆ ይዤ በመካከላቸው ቆምኩ፡፡ጋሽ ይታየው የቀዳሁለትን ውስኪ ወደ አፉ ደፋና ሳይውጠው ለደቂቃዎች ቆየ ፡፡ሰውየውና እኔ ግራ ተጋብተን አስተዋልነው፡፡የጉንጩ ውስኪ ሳይውጥ ሀውልት መስሎ ለደቂቃዎች ከቆየ በኃላ እየሳሳ ወጠው፡፡
‹‹በሰላም ነው ጋሽ ይታየው?›› አልኩት አይኔን ከእሱ ሳልነቅል፡፡
‹‹አይ በሰላም ነው ይሄን መሳይ ውስኪ እስከ ዛሬ አምስት አመት የምጠጣበት አጋጣሚ ስለሌለ ሰላም እያልኩትም እየተሰናበትኩም ነው፡፡›› አለኝ ቀሪውን እየጨለጠ፡፡
‹‹የዛሬ አምስት ዓመት ውስኪ እንደምትጋበዝ በምን አወቅክ?›› አለ ሰውየው ፡፡
‹‹ያው የዛሬ አምስት አመትም ምርጫ እንደሚኖር በመገመት ነዋ፡፡›› አለ ጋሽ ይታየው በለሆሳስ፡፡
ይናደዳል ያልኩት ሰውዬ ጋሽ ይታየውን በአንድ እጁ አቅፎ በአንድ እጁ የድራፍት ጠርሙሱን እንደያዘ በሳቅ ተርገፈገፈ፡፡
‹‹ድገመው ይሄንን አስቂኝ ሰው..››
የታዘዝኩትን አደረኩ፡፡ጋሽ ይታየው መላ አካሉ ሲወግ ይታወቃል፡፡ሰውየውና ጋሽ ይታየው ከደቂቃዎች በፊት ሳይሆን ለአመታት የሚተዋወቁ ለመምሰል አፍታ አልወሰዱም፡፡
‹‹እኔ እኮ ገዢውን ፓርቲ በጣም ነው የምወደው፡፡›› ጋሽ ይታየው ጀመረ፡፡‹‹በጣም ነው የምወደው፡፡ የመጀመሪያ ልጄን ዘላለም ያልኩት የገዢውን መንግስት ጠባይ በማየት ነው፡፡ዘላለም እንደማይወርድ በመገመት ነው ዘላለም ያልኩት፡፡››
ሰውየው ከቅድሙ አስበልጦ ተርገፈገፈ
‹‹ድገመው …ድገመው ውስኪ››
ጋሽ ይታየው ቀጠለ፤ ‹‹ እኔ ከሚስቱ በተጣላ ቁጥር የፖለቲካ ፓርቲ የሚያቋቁም ሰው ሰልችቶኛል፡፡የሀገራችን ተቀዋሚዎች ገና ይቀራቸዋል፡፡አይናማ ጓደኞቼ እንደነገሩኝ ከሆነ አብዛኞቹ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እጅግ ቀጭኖች ናቸው፡፡ፓርቲውን የመሰረቱት ሊታገሉበት ሳይሆን ሊደልቡበት ነው የሚመስለው፡፡››ሳውየው በሳቅ ከወንበሩ ላይ ሁለቴ ተንሸራቶ ሲወድቅ ይታየኛል፡፡
‹‹ድገመው… ውስኪ ድገመው!››
ትዕዛዝ እፈጽማለሁ፡፡
ይታየው ቀጠለ፣‹‹ይህ መንግስት ሺ ዓመት ቢነግስ ደስታየ ነው፡፡ይሄ መንግስት የሰራውን ማን ሰራ፡፡አሁን የባለፈው ባቡር በቀላል የሚታለፍ ነው? በፍጹም፡፡ትንሽ ቅር ያለኝ ባቡሩ በኤሌክትሪክ ሃይል ነው የሚሰራው መባሉ ነው፡፡እንደው ከሳሪስ ሲበር የመጣው ባቡር ስቴዲየም አካባቢ የመብራት ተረኛ ሆነው ከጠበቁት ጉድ መሆኑ ነው፡፡እስቴዲየሙ አናት ላይ ባቡሩ ከቆመ ምን ይኮናል፡፡ፓራሹት ያለው ብቻ ቢወርድ ነው፡፡ሌላዋ በተቀመጠችበት አራት ግንቦት ሃያ ማለፉ ነው፡፡
ከምኒሊክ ባቡር ጋር ሳነጻጽረው እኒኛዎቹ ባቡሮች አነስ አነስ አሉብኝ ግልገል ባቡር ነው እንዴ ቻይና የሸጠችላችሁ?
በተረፈ ባቡሩ ስራውን የጀመረው ምርጫው ሲጠጋ መሆኑ ጥሩ ነው፡፡ዘጠና ሰባት ላይ አውቶብስ ብቻ ነበር የተሰባበረው ዘንድሮ አማራጭ አለን ማለት ነው፡፡እውነት ለመናገር ግን ገዢው መንግስት ሰጦ መቀበል ሳይሆን ወስዶ መመለስ በሚለው ዕቅዱ እያሞኘንም እያስገረመንም ነው፡፡ ሶስት ወር ውሃ ጠፍቶ አንድ ቀን ሲለቀቅ ተመስገን አንለዋለን፡፡አራት ቪላ ከሚያሰራው ቦታችን አፈናቅሎ የሃብታም ኩሽና የማታክል ኮንደሚኒየም ሲሰጠን እናመሰግነዋለን፡፡አሁን ደግሞ ለሀያ ምናምን ዓመት ጸሀይ ላይ አሰልፎን ሲያበቃ ጥቂት ፍርጎ ስላሳየን በደሉን እንሰርይለታለን፡፡ ለዚህ ነው ገዢውን ፓርቲ የምደግፈው ፡፡ ዳቦህን ቀምቶ አቆይቶ አስርቦ ሲመልስልህ ኬክ እንዲመስልህ ያደርጋል፡፡ለዚህ ነው ገዢውን መንግስት የምመርጠው፡፡››
ሰውየው ከዚየ ሁሉ ወሬ ውስጥ ጋሽ ይታየው ገዢውን መንግስት እመርጣለሁ ማለቱን ብቻ ነጥሎ እንደሰማ አምኛለሁ፡፡ለዛ ነው አሁንም ‹‹ውስኪ ድገመው …›› ብሎ የጮኸው፡፡
ሰውየው ከጋሽ ይታየው መድረኩን ተቀበለ፤‹‹ እንደ አንተ ያለ ምርጥ ሰው ሳገኝ ደስ ይለኛል፡፡ከእኛ ጋር ለመጓዝ የወሰነ ሰው ጀግና ነው፡፡አዳሜ ግንቦት ሰባት ይመጣልናል እያለ ያወራል፡፡የታለ ግንቦት ሰባት? እንደ ጀማሪ አትሌት ማሟሟቅ ከማብዛት ሌላ የት አለ?
ተቃዋሚዎች የምሁራን ስብስብ ናቸው ይሉናል፡፡ውሸት ነው፡፡የእኛን ፓርቲ የሚያል የምሁር ስብስብ አለ፡፡ደስ ካለን ተምረን ደስ ካላለን ሸምተን ዶክተርና ፕሮፌሰር መሆን እንደማያቅተን ከእኛ በላይ ማን አሳየ?
የውጭ ሚዲያዎች ሁሌ ስማችንን ያጠፉናል፡፡አሰራችሁ ፣ገደላችሁ ፣አሰደዳችሁ ይሉናል፡፡አሁን እኛ የሰራነው IsIs ከሰራው ስራ ጋር ይወዳደራል?
ምርጫ ቦርዱ ወገንተኛ ነው ይላሉ፡፡ውሸት ነው፡፡ዋነኛ ዓለማው የእኛ ፓርቲ እንዲያሸንፍ መርዳት መሆኑ ነው ወገንተኛ ያሰኘው? ሌላው ይቅር ለምን ይሳደባሉ፡፡መርጋ በቃናን ምርጫ በቃና አሉት፣ብሩክ ከበደን ብኩን ከበደ አሉት፡፡ ይሄ ይቅር እሺ አዳዲስ ምሳሌያዊ ንግግሮችን ሁሉ ፈልስሰፈዋል፡፡ እኔ እንኳ ከሰማኃቸው ውስጥ
‹‹በእኛ ጥርምስ አልተሳቀ አለ ትዕግስቱ አወሉ››
‹‹ዶክትሬትስ ምንድር ነው እኔስ ምንድር ነኝ አለ ቆስጠንጢኖስ›
‹‹እየመጣሽ ተኝ አለ ዘማሪ ተከስተ››
የሚሉት በአንድም ሆነ በሌላው ከፓርቲው ጋር ይገናኛሉ፡፡
ለማንኛውም እንዳንተ ያለው ከእኛ ጎን በመሰለፉ ደስተኛ ነኝ፡፡በዚሁ አጋጣሚ እየመራሁ እቤትህ ድረስ ባደርስህ ደስ ይለኛል፡፡ለዚህ ሁሉ ውለታዬ ግን የምርጫ ድምጽህን ለእኛ ፓርቲ እንደምትሰጥ አልጠራጠርም፡፡ አየህ አሁንም የተናነቁን ፓርቲዎች አሉ፡፡እስከ ግንቦት እነሱን የሚለቅም በሽታ ካልመጣ ያሰጉናል፡፡ እንዳንተ ያለውን ሰው የምንፈልገው በእንዲህ ያለ ጊዜ ነው፡፡››
ጋሽ ይታየው ሞቅ እንዳለው ያስታውቃል፡፡እቤቱ የሚያደርሰው ሰው በማግኘቱ የበለጠ ልበ ሙሉነት ተሰምቶት ተጨማሪ መለኪያዎችን ወረወረ፡፡ከደቂቃዎች በኃላ የሰውየውን ክንድ በግራ የገዛ በትሩን በቀኙ ይዞ ተነሳ፡፡
ከተቀመጡበት እስከ በሩ ለመድረስ ሲጥሩ ሶስት ጊዜ ወደቁ፡፡
ጋሽ ይታየው ብልጭ ሳይልበት አልቀረም፡፡
‹‹እመራሃለሁ አላልክም እንዴ?››
‹‹እና እየመራውህ እኮ ነው፡፡››
‹‹እንቅፋት ያለበትን ቦታ እየመረጥክ ነው እንዴ የምትረግጥ!››
‹‹አይ እንግዲህ ጸባይህን አሳምረህ ትመራ እንደሆነ ተመራ››
ይሄኔ ጋሽ ይታየው አላስቻለውም፡፡ ክንዱን ከሰውየው መነተፈና ተወራጨ፡፡
‹‹እንዴውም ከአንተ ጋር መሄድ አልፈልግም!››
ሰውየው በንዴት ጋሽ ይታየውን ከላይ እስከ ታች ገረመመው፡፡አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ድንፋታዎችን ካሰማ በኃላ ከድራፍት ቤቱ ወጣ፡፡ጋሽ ይታየው ለደቂቃዎች ሌላ አማራጭ እያሰበ ተገተረ፡፡ጭንቀቱ ገባኝ እንዲህ ሰክሮ በተቆፋፈረው መሬት ላይ እንደምን ራሱን ችሎ መጓዝ ይቻለዋል? ጋሽ ዘሪሁንን ጭንቀቱ የገባው ይመስል ከመቀመጫው ተነሳና የአይነስውሩን እጅ ያዘ፡፡
ከመውጣታቸው በፊት በተረብ ሸኘኃቸው
‹‹ከምርጫ የተባረረ ፓርቲ እንዲመራህ ፈቀድክ..?››
ጋሽ ይታየው መልስ አላጣም ‹‹ መምራት ማለት ቤተመንግስቱን መያዝ አይደለም፡፡የህዝብን ልብ ማሸነፍ ነው…››
የጋሽ ዘሪሁን ተስፋ መቁረጥ ከፊቱ ላይ ሲሸሽ ተመለከትኩ፡፡ተያይዘው ሲወጡ ታዩኝ ከአይኔ ከመራቃቸው በፊት ወደ ምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት ዞሮ ጋሽ ይታየው ተናገረ፡፡
‹‹ደህና ደሩ ሙታን…››
አምሽተው የሚሰሩት የጽ/ቤቱ ሰራተኞች ሲረግሙት ይሰማኛል፡፡
‹‹እንደ ፓርላማው ጨለማ ያግባህ!››
‹‹እንደ አቶ ትዕግስቱ ባዶ ቢሮ ያታቅፍህ..››
‹‹እንደ ሬዲዬ ፋና ቀፎህ ብቻ ይቅር…››
የአለቃቸው ድምጽ ርግማኑን አቋረጠው፡፡
‹‹ወደ ስራ ተመለሱ…ምን ላይ ነበር ያቆምነው ? አዋ!ሰማያዊዎችን ደግሞ ለስንት እንክፈላቸው?››
…
ተጻፈ በሀብታሙ ስዩም
No comments:
Post a Comment