Friday, February 6, 2015



#Abebe Tolla
በአሁኑ ሰአት፤ ኢህአዲግ ካደረገን ነገሮች ሁሉ የከፋው ስለየትኛው በደል አንስተን ስለየትኛው እንተወው፤ ስለማን አውርተን ስለማን ይቆይ እንበል፤ ስለየትኛው ችግር ተናግረን የትኛውን እናሳድረው... በሚሉ አጣብቂኝ ውስጥ መክተቷ ሳይሆን አይቀርም።

በየቀኑ በደል በየቀኑ ክፋት በየቀኑ ሰቆቃ...

እጅግ ወዳጃችን የሆነው ተመስገን ደሳለኝ በአሁኑ ሰዓት የታሰረው አልበቃ ብሎ ምግብ እንዳይገባለት ጠያቂም እንዳያየው ተከልክሏል። ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ሲያሰቃየው የነበረ የኩላሊት ህመም ህክምና እንዳያደርግ ተከልክሎ ከዝዋይ ቂሊጦ ከቂሊጦ ዝዋይ ሲመላልስ ሰንብቷል። ርዮት አለሙ ሀመሟ ምን ቢከፋ መንግስት በርህራሄ ሊያያት ቀርቶ ጭራሽ በስቃይዋ ደስታው ጣራ ሳይነካ አይቀርም።


ስማቸውን ሰምተን እንኳ የማናወቀው እነ ሂሩት ክፍሌ እና ዘሪሁን ገብረእግዚአብሄር ምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ቃሊቲ እና ቂሊጦ ይወቁት። እነ ኦልባና ሌሊሳ እና በቀለ ገርባ እንዴት ያለ የስቃይ ጊዜ እያሳለፉ ነው... የሚለውን ተናገረን መጨረስ ከባድ ነው።

አቤል ዋበላ ማዕከላዊ ''ምርመራ'' ሲደረግ የተመታው ጆሮው ክፉኛ ተጎድቶ በቂ ህክምና ማገኘት ይቀርና ባለፉት ሰሞናት በውሻ ሰንሰለት ታስሮ መሰንበቱን ሰምተናል። ማሂ እና ኤዶም ''በአዳኝ'' ካሜራዎች ፈግግታቸው ቢያጽናናንም እንዴ ያለ አያያዝ እንደተያዙ የሚያውቀው የቃሊቲው ሚካኤል ብቻ ነው።

የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት እነ አቡኬ እንዴት ናቸው... የሚለውን ማን ዘርዘሮ ይጨርሳል!

እነ የሺዋስ አሰፋ ዳንኤል ሃብታሙ እና አብርሃ ደስታ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ አውርተን ለመጨረስ ብንነሳ አባይን በጭለፋ ነው።

እስክንደር ነጋ አንዱለም አራጌ አበበ ቀስቶ የደረሰባቸው እስራት ብቻ አይደለም። በየቀኑ ይህ ነው የማይባል አበሳ በታሰሩበት እስር ቤት ውስጥ እያሳለፉ ነው።

ትላንት እጁን የተሰበረው ስለሺ ሀጎስ እጁ በቀዶ ጥገና ህክምና እያገገመ መሆኑን ብንሰማም የተሰበረለት የሀገሪቷ እና የመንግስታችን ችግር ግን እርሱ ድኖም ሲነሳም የሚጠግን አይደለም። ልዕልና ጉግሳ ከደረሰባት ዱላ አገግማ ሊሆን ይችላል፤ ነፈሰ ጡሯ አጥናፍወርቅ ያለርህራሄ ያረፈባት ዱላ ተርፋ በሆዷ ያለውን ልጅ ከወራት በኋላ በሰላም ተወልድ ይሆናል፤ ያረገዝነው የፍትህ እና መልካም አሰተዳደር ጽንስ ግን መቼ እንደሚወለድ ግራ እየገባን ነው።

ባጠቃላይ መንግስታችን በበደል ላይ በደል እየደረበ በችግር ላይ ችግር እየፈጠረ እንደ እሳት አደጋ ሰራተኛ አንዱ ጋ ሲቃጠል ወደ አንዱ ስንሮጥ ሌላው ጋ ሲያነድ ድረሱልኝ ብለን ስንጮህ፤ የትኛውን አንስተን የትኛውን እንደምንተወው ይጨንቃል።

ዘዴው እሳቱ መንግስታችን እዚህም እዛም እየለኮሰ የሚያቃጥለውን ነገር እንዲያቆም በጥቅሉ መጠየቅ ነው እንጂ የተናጠል ጩሀት የትም የሚያደርስ አልሆነም። በጅምላው አበሳችን የሚቀንስበትን ዘዴ መቀየስ ካልቻልን አደጋ ላይ ነን። ላጠቃላይ ችግራችን፤ ጸሎተኛው በጸሎቱ፣ ሰላማዊ ታጋዩ በየስልቱ፣ ታጣቂው በቆራጥነቱ.... ሁሉም በየዘርፉ አቃጣዩን መንግስት መለብለቡን እንዲያቆም ለማድረግ ካልተጋን በቀረ.... አንዱን ጥሎ አንዱን አንጠልጥሎ መሄድ ከባድ ነው!

No comments:

Post a Comment

የምጣዱ እያለ የእንቅቡን፤ የእርስ በርስ ግጭት እና የመንግስት ምላሽ

በያሬድ ሃይለማሪያም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አሁንም ግጭቶች መበራከታቸው እና መፈናቀል መቀጠሉ የአገራችንን ፖለቲካ አሳሳቢ እያደረገው እና አገሪቱንም ወደ ችግር ውስጥ እየከተታት ይመስላል። መንግስት ለችግሮቹ የሚሰ...