Sunday, January 18, 2015

አዛኝ ቅቤ አንጓች!!!

ለራዲዎ ፋናና መሰል ኢህአዲጋዊ መገናኛ ማእከላት
--------------------------------------------------------------------------------
በቅድሚያ በነዚህ ራዲዮ ፋናና ኢቢሲን መሰል የመገናኛ ብዙሀን ማእከላት የምትሰሩ ግለሰቦች ትክክለኛ ጋዜጠኛና የጋዜጠኝነትን ትምህርት የወሰዳችሁ ናችሁን??? ……እኔ ግን አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም በአንዳችሁም እንኳ ላይ የጋዜጠኝነትን ስነ-ምግባር አላየሁባችሁምና ነው፡፡ …..ምናልባት የጋዜጠኝነት ስነ-ምግባሩ የሚገለጥላችሁ ከኢህአዲግ በረት ወጥታችሁ ወደ ውጭ ስትሰደቱ ይሆን??? …… ይህ ከሆነም ጋዜጠኛ አደላችሁም፡፡ ምክንያቱም ጋዜጠኛ ማለት እጅግ ፈታኝ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንኳ ሁኖ ለህብረተሰቡና ለሚያገለግለው ህዝብ ተአማኒና ከተፅእኖ ነፃ የሆነ መረጃ ማድረስ የሚችል ነው፡፡


እንደው አንዳንዴ ሳስበው ጋዜጠኛ አደላችሁም ብዬ አስረግጨ እናገራለሁ፤…..ምናልባት እነዚህ ሰዎች ኢህአዲግ ከየቦታው ማንበብና መፃፍ የሚችሉ ሰዎችን ሰብስቦ ብርሸለቆና ፆላይ በመሳሰሉት ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች ለሶስት ወር ለብለብ አድርጓቸው የመጡ የውሸት አምባሳደር ናቸው እንዴ ብዬ አስባለሁ!!! ……ይኸን ሁሉ የምለው ያለምክንያት አይደለም፡፡ እናንተ ማለት ከእውነት ይልቅ ለውሸት የቀረባችሁ፤ ….ለጋዜጠኝነት ክብር ሳይሆን ፍርፋሪ ለሚጥልላችሁ ገዢ ፓርቲ ፕሮፓጋንዳ የቆማችሁ፤…..የህዝብን እርሀብና ብስቁልና በእናንተ ጥጋብና ምቾት የምትመዝኑ፤……… ሙያዊ ስነምግባራችሁ የሚላችሁን ሳይሆን አድርጉ የተባላችሁትን የምትፈፅሙ፤…….በህዝብ እንባ፤በህዝብ ስቃይ፤በህዝብ ደም የተሳለቃችሁ …… ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት መፋጠን ደንቀራ የሆናችሁ፤ ……ታሪክ ለፍርድ መዝግቦ ያኖራችሁ ዋሾዎች በመሆናችሁ ነው፡፡ ……. እንደው ይህን ካልኩ ዘንዳ ራዲዮ ፋና ስለተባለውና እራሱን የግል ነኝ ከሚለው፤የስርአቱ ፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ የትናንትና ዘገባ የተፈጠረብኝን ግርምት ላጫውታችሁ፡፡

ሚዲያዊ ፕሮፓጋንዳ ማለት ያው ገዢው መንግስት በተቃዋሚዎች ላይ የፖለቲካ ትርፍ ያስገኝልኛል ብሎ ያሰባቸውን ፕሮግራሞችና ዝግጅቶችን በሚመች ሁኔታ ማቅርብና የህዝብን እይታና አመለካከት መቀየሪያ ድስኩር ነው፡፡ በሀገራችን ያሉ ሚዲያዎችም ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚያስችል ሁኔታ በዚህ ተግባር ተጠምደው፤የህዝብ ድምፅ ሳይሆን የኢህአዲግ ፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ ሲሆኑ እናያለን፡፡ ትናንት የገረመኝ አንድ ነገር ሬዲዮ ፋና ተብዬው የአንድነት ፓርቲን ለዚህ ግብአት ለማድረግ ሁለቱ የአንድነት ፕሬዝዳንቶች የተፈጠረባቸውን አለመግባባት ……ምናምን እያለ ሲደሰኩር ሰማሁና አዘንኩ፡፤ ….አንድ ቀን እንከዋ ስለፓርቲዎች ጥንካሬና እንቅስቃሴ ዘግበው የማያውቁት መገናኛ ብዙሀን፤……ስለፓርቲዎች በጎ ጎን ለመዘገብ ሰዓት የሚያጥርባቸው መገናኛ ብዙሀን፤…….ለአንድ የማፊያ ድርጅት ፕሬዝዳንት ብለው የአንድነትን ስም ለማጉደፍና በህብረተሰቡ ዘንድ ብዥታ ለመፍጠር ሰፊ የአየር ሰዓት ሰጥተው ሲዘግቡና ወደፊትም እንደሚሰሩ ሲናገሩ ስሰማ እጅግ አፈርኩ፡፡ ተሸማቀኩ፡፡

ቆይ ሬዲዮ ፋና ህጋዊውና በአቶ በላይ ፈቃዱ የሚመራው አንድነት ፓርቲ በ01/05/07 በምርጫ ቦርድና በኢህአዲግ እየተፈፀመበት ያለውን ደባ አስመልክቶና በሌሎች ሂደቶች ላይ የሰጠውን የአቋም መግለጫና ማብራሪያ ለምን እንደዚህ በሰፊው አልዘገበውም፤…….አንድነት በምርጫ ቦርድ የተፈፀመበትን ህገ-ወጥ ተግባር አስመልክቶ ለእያንዳንዱ የሚዲያ ተቋም የሰጠውን የደብዳቤ ልውውጥ አስመልክቶ እንደመርማሪ ጋዜጠኛ ለህዝብ ሰፊ ውይይትና መግለጫ ለምን አላወጡም፤……..አንድን ህገ-ወጥ የማፊያ ቡድን አንድነት ፓርቲ ብሎ ማቅረብስ በህግም ሆነ በሞራል የሚያስከትለውን ችግር እንዴት አልተረዱም፤……….ለሀገር ሁለንተናዊ ግንባታና እድገት ለፍትህና መድብለ ፓርቲ ስርአቱ መጎልበት ያልተጠቀሙበትን ሚዲያ የገዢውን ፕሮፓጋናዳ ለማስፈፀምና የመድብለ ፓርቲ ስርአት ግንባታ ጉዞውን ለመጎተት ሲጠቀሙበት፤….ፓርቲዎችን ለማዳከምና በህዝብ ዘንድ ተአማኒነት ለማሳጣት ሲጠቀሙበት ፤……..እያየን ከኢህአዲግ መንግስት ባልተናነሰ፤…ምርጫ ቦርድ ከሚፈፅመው ህገ-ወጥ ድርጊት ባልተናነሰ ለኢትዮጵያውያን የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ መጓተትና፤….የአንባገነኖች መንገስ ብሎም በህዝብ ዘንድ ለሚደርሰው ስቃይና መከራ ሁሉ እነዚህ የሚዲያ ተቋማትና በውስጣቸው የታጨቁት እልፍ ተላላኪ የውሸት አምባሳደሮች ግንባር ቀደም ተሰላፊዎች መሆናቸውን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያውቀው ይገባል፡፡ …….

No comments:

Post a Comment

የምጣዱ እያለ የእንቅቡን፤ የእርስ በርስ ግጭት እና የመንግስት ምላሽ

በያሬድ ሃይለማሪያም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አሁንም ግጭቶች መበራከታቸው እና መፈናቀል መቀጠሉ የአገራችንን ፖለቲካ አሳሳቢ እያደረገው እና አገሪቱንም ወደ ችግር ውስጥ እየከተታት ይመስላል። መንግስት ለችግሮቹ የሚሰ...