Thursday, December 4, 2014

ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት ዳገት ላይ ይለግማል ይባል የለ የሕወኃት መራሹ የኢሕአዴግ መንግስት ሀገራችን ኢትዮጵያ ከአለም በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ላይ መሆንዋን በዓለም ምርጥ ኢኮኖሚስቶችን እየጠቃቀሰ እገሌ ተደነቀ እገሌ ደግሞ ከኢትዮጵያ ተማሩ ሲል አሳሰበ ሲል ነጋ ጠባ በተደጋገመ አሰልች ፕሮፓጋንዳ ቁርስና ምሳ እያበላ ያጠግበናል።
እርግጥ ነው ጥቂቶቹ ከብዙሀኑ ያለ ምንም ይሉንታ በዘረፉትና በሰበሰቡት መጠነ ሰፊ ሀብት ማስቀመጫ የጠበባቸው መሆኑን አይተናል፣ከሁለት አስርቱ ዓመታት በፊት የምትኮሳ ደሮ በግቢያቸው ያልነበራቸው ተራ ሰወች ከስርአቱ ጋር በዝምድና በአምቻ ጋብቻ በደቀ መዝሙርነት ወይንም ይህ ሁሉ ያልተሳካላቸው ደግሞ ጡት ተጣብተው ከዘመኑ መሳፍንቶች ጋር ተጠግተው ሚሊዮኔር ለመሆን ችለዋል አጠቃላይ የማኅበረሰባችን ማኅበራዊ ግንኙነት ሲዳሰስ በአንድ በኩል ሰማይ ጠቀስ ጌትነት በሌላ በኩል አንጀት የሚበጥስ ድህነት ሆኗል።
ስለ በለፀጉት ጥቂቶቹ ትተን ለተፈናቀሉ በገዛ ሀገራቸው የትም ለተጣሉ አሮጋውያን፣ሕፃናትና የምታጠባው ህፃን ጡቷ በረሀብ ጠውልጎና ደርቆ የምትወደው ልጅ ደረቷ ላይ ለሞተባት እናት ወይም እርሳው ቀድማ ሞታ የበድን ገላዋን እየደበደበ ለሚያለቅሰው ሕፃንስ ማን ይናገር?
በሉ ሀገር አደገ ሕዝብ ተመነደገ ብላችሁ በእድር በለቅሶ በሰርግና በየትኛውም በተገኘ አጋጣሚ ሁሉ የኢሕአዴግን ጥሩምባ በትእዛዝ የምትነፉ ሁሉ መልስ ስጡን ይህ ስርአት ከማን ነጥቆ ለማን ሰጠ ስንቱን ገድሎ ስንት አዳነ ለምንስ ከእርሱ የተሻሉትን ሁሉ አግልሎ ደደብ ደንቆሮን ያከብራል ለምንስ ይሆን ሀገር ወዳድን ጠልቶ ከሀዲን ያነግሳል?
ግራም ነፈሰ ቀኝ የህዝብ ስቃይና ሮሮ መግላሊቱን ፈንቅሎ ከሚፈነዳበት ወቅት ላይ መድረሱ እውነት ነው ሕዝባዊው ማእበልም አይቀሬ ሆኗል ሁሌም እናጭበረብረዋለን ብላችሁ የምታምኑት የዓለም ማኅበረሰብም እድሜ ለሀገራችን ጀግኖች እንጅ የደበቃችሁትን እውነታ እየገላለጠ ሚስጥራችሁ ሁሉ በአደባባይ ገመናችሁ ፀሀይ እየሞቀ ነውና የትናንቱ የማጭበርበር ሰፊ እድል ተዘግቷል፣ስለዚህ በምርጫ 2007 ተቃዋሚን ከማዋከብ ከማሰርና ከመግደል ከማሳቀቅና ማሸማቀቅ የምታገኙት ትርፍ ቢኖር በእልህ ዳር የቆመውን ሁሉ ወደ ማህል እየገፋችሁት ነው እና ትርፉ 0+0 ነው፣ አይጠቅምም ይቅር።

No comments:

Post a Comment

የምጣዱ እያለ የእንቅቡን፤ የእርስ በርስ ግጭት እና የመንግስት ምላሽ

በያሬድ ሃይለማሪያም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አሁንም ግጭቶች መበራከታቸው እና መፈናቀል መቀጠሉ የአገራችንን ፖለቲካ አሳሳቢ እያደረገው እና አገሪቱንም ወደ ችግር ውስጥ እየከተታት ይመስላል። መንግስት ለችግሮቹ የሚሰ...