Sunday, January 14, 2018

እስረኞችን መፍታት የሕዝቡ አንዱ ጥያቄ እንጂ ብቼኛውና የመጨረሻው ጥያቄ አይደለም!


ሕዝብ ጠንክሮ ከታገለ በመጨረሻ ላይ የድሉ ባለቤት መሆኑ የማይታበል ሃቅ ነው።ለዚያ ወሳኝ ደረጃ ለመድረስ በሚያደርገው የትግል ጉዞ መጠቃትና ማጥቃት፣ ድል መሆንና ድል ማድረግ ተፈራራቂ ክስተቶች ናቸው።እስከ አሁን ድረስ ለ27 ዓመታት በተጓዘበት የትግል ጎዳና የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ታላቅ ድል የተጎናጸፈበት ጊዜ ቢኖር በ1997 ዓም በተካሄደው ምርጫ ያገኘው ውጤት ነበር።ያ ድል ግን በአረመኔዎቹ የወያኔ አፋኝ ቡድንና ባጫፋሪዎቹ ተባባሪነት ተክዶ እስከ አሁን ድረስ ላለው ለበለጠ ስቃይና ጭቆና ዳርጎታል።ግፍ በበዛ ቁጥር የሕዝቡ እምቢባይነት እንደሚያገረሽ ያልተገነዘበው እብሪተኛው ቡድን የልብ ልብ ተሰምቶት አገዛዙን ዘላለማዊ ለማድረግ ባደረበት ቀቢጠ ተስፋ ታውሮ ዘረፋውን፣መግደሉን፣ማሳደዱን ማሰሩን በስፋት ተያያዘው፤ያም በመሆኑ የግፉ ጽዋ ሞልቶ መፍሰስ ከጀመረ ከሁለት ዓመታት በላይ ሆኖታል። የሕዝቡ ትግል ከዳር እስከዳር ተቀጣጥሎ የለውጥ ማዕበል ሆኖ አሁን ባለስልጣኖቹን ከከፍተኛ ስጋት ላይ ጥሏቸዋል።በዚህ የሕዝብ ቁጣ የተደናበረውን የወያኔ መራሹን ቡድን የሚይዝ የሚለቀውን አሳጥቶታል።ችግሩን በዝግ ስብሰባ ያሶግደው ይመስል አንድ ጊዜ መቀሌ፣ሌላ ጊዜ አዲስ አበባ በሚያካሂደው ስብሰባ እርስ በርሱ ከመጋጨትና ከመዘላለፍ የተለዬ ፣ የሕዝቡን ቁጣ የሚያበርድ፣ጥያቄውን ከሚመልስ አንዳችም ውሳኔ ላይ አልደረሰም።ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አንድ ጊዜ የማስፈራሪያና ዛቻ የተሞላበት በሌላ ጊዜ ለሰላም ተቆርቋሪና አሳቢ የሚመስል የማጭበርበሪያ መግለጫ ከሚለፍፍበት ደረጃ ላይ ደርሷል።



ወያኔ በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ብዙ ሰው ይታሰራል፣ይገደላል፣ይሰደዳል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሰጠው መግለጫ አስገዳጁ የሕዝቡ ተቃውሞ እንጂ ወያኔ ሰብአዊ ስሜት አድሮበት አይደለም።እንደ ወያኔ ፍላጎትና ምርጫ ቢሆንማ ኖሮ በተካነበት መንገድ ሁሉንም በጭስ አፍኖ በጨረሳቸው ነበር።ምናልባት ወደፊት እስረኞችን እንዲፈታ ከውስጥም ከውጭም ግፊት ቢበዛበት የሚለቃቸው በራሱ ምርጫ አደገኛ ይሆናሉ ብሎ የማያስባቸውን፣በጥርጣሬ ያሰራቸውንና ምናልባትም የተወሰኑ በውጭና በአገር ውስጥ ድጋፍና እውቅና አላቸው ብሎ ያሰባቸውን የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ግለሰቦች ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት አያቅትም። አንድም ሰው ቢሆን መፈታቱ አይጠላም።በወያኔ ስሌት በዚህ ቁንጽል እርምጃ እራሱን ለተሃድሶ የተዘጋጀ አድርጎ ለማሳዬት ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማታለል የሚሞክርበት ስልት ለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ነገ ደግሞ የፖለቲካውን ምህዳር አሰፋሁ በሚል ማጭበርበር እራሱ የቀፈቀፋቸውን በስመ ተቃዋሚ በምርጫ ወቅት ድምጽ ለመሻማት የሚያሰልፋቸውን፣እራሱ ያረቀቀውን ሕገ-መንግስቱን የተቀበሉ አጋሮቹን በፓርላማ ውስጥ የተወሰነ ወንበር እንዲያገኙ የማድረግ ስልት ሊጠቀም እንደሚችል ማሰብ የወያኔን ተፈጥሮ ለሚያውቅ እንግዳ አይሆንበትም።

No comments:

Post a Comment

የምጣዱ እያለ የእንቅቡን፤ የእርስ በርስ ግጭት እና የመንግስት ምላሽ

በያሬድ ሃይለማሪያም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አሁንም ግጭቶች መበራከታቸው እና መፈናቀል መቀጠሉ የአገራችንን ፖለቲካ አሳሳቢ እያደረገው እና አገሪቱንም ወደ ችግር ውስጥ እየከተታት ይመስላል። መንግስት ለችግሮቹ የሚሰ...