Tuesday, April 11, 2017

የህዝብ ጠላት የለኝም!

ዘረኝነትን ለማጥፋት ዘረኞችን መሳደብ አያስፈልግም። ዘረኛን ለማሸነፍ ዘረኛን ማሳመን እንጂ ዘረኛን ማጥላላት ልክ አይደለም። ዘረኛን ለማሸነፍ ዘረኛውን ማሳመን፣ ለማሳመን መረዳት፣ ለመረዳት በትዕግስት ማዳመጥ። ሲሰድብህም ታገሰው፣ ተረዳው። ዘረኛ ነው ብለህ ብታጥላላው ግን አንተ ራስህ የባስክ ዘረኛ ነህ። ዘረኞችን ማሸነፍ የሚቻለው ዘረኛ በመሆን ሳይሆን ወይ በማጥላላት ሳይሆን ራሳችን ከዘረኝነት በመውጣት ነው። ዘረኛን ማጥላላትና መሳደብ ዘረኝነትን ማስፋፋት እንጂ መከላከል አይደለም።


(ይቅርታ "ዘረኝነት" ያልኩት "ጎሰኝነት" ለማለት ፈልጌ ነው። ኢትዮጵያውያን የተለያየ ጎሳ እንጂ የተለያየ ዘር የለንም።)

ጥላቻን ማስወገድ የምንችለው ፍቅርን በመስበክ እንጂ በመጥላት አይደለም። ጥላቻ ሰባኪዎቹን መጥላት ጥላቻን ያበዛል እንጂ አይቀንሰውም። እነ እገሌ ጠላቶቻችን ናቸው እያልክ አትስበክ። ሲጀመር ህዝብ የህዝብ ጠላት የለውም። ሲቀጥል የህዝብ ጠላት ስርዓት ነው። ለህዝብህ የምትቆረቆር ከሆነ የህዝብን ጠላት የሆነውን ስርዓት አስወግድ እንጂ ህዝብህ ከሌላ ህዝብ ጋር ለማጣላት አትሞክር።

"የትግራይ ህዝብ ጠላታችን ነው" ይሉና "የትግራይ ህዝብ ምን አደረጋቹ?" ሲባሉ "አታዩም እንዴ ህወሓት የሚፈፅምብን በደል!?" ይሉሃል። "የአማራን ህዝብ ለማስደሰት አትስራ። አማራ ጠላታችን ነው" ይሉኛል። "አማራ ምን በደላቹ?" ስላቸው "ምኒሊክ፣ ሀይለስላሴ ወዘተ እንዲህ አደረገን" ይሉኛል።

የምኒሊክ ስርዓት ስለበደለው በአማራ ህዝብ ያሳብባል። የህወሓት ስርዓት የበደለው በትግራይ ህዝብ ያሳብባል። በዳዩ ምኒልክ እያለ አማራ በደለን ማለት ምን ማለት ነው? ምኒሊክ አማራ እንጂ የአማራ ተወካይ አይደለም። ብትፈልግ ምኒልክን አትጠላም? ከስልጣን አታባርርም? ህወሓት ከበደለህ ህወሓትን አትጠላም? ህወሓት የትግራይ ህዝብ ወኪል አይደለም። ስርዓት ሲበድልህ ስርዓቱን መጥላት ትችላለህ። ህዝብ ግን አልበደለም።

ስርዓት ሲበድልህ ሀገርህን ትጠላለህ?! ስርዓትና ሀገር አንድ አይደሉም። ስርዓቱ ቢበድልህና ቢያስጠላህ አስወግደው። ሀገርህ ግን ምን በደለች? ሀገር በደል ልታደርስብህ አትችልም። የማይመች ስርዓት ወይ ገዢ ወይ መንግስት ካለ ግን አስወግደውና የሚመችህን አስተዳደር መስርት። ስርዓት ማስወገድ ስላቃተህ ብቻ ህዝብንና ሀገርን መጥላት ክሽፈት ነው።

የህዝብና የሀገር ጠላት የለኝም። ጠላቴ አንድ ነው፤ የፖለቲካ ስርዓቱ። እሱም የተሻለ አማራጭ ፖሊሲና የሐሳብ መንገድ በማቅረብ አሸንፈዋለሁ። ፈጣሪ ሀገራችንና ህዝባችን ይባርክልን። ጨቋኝ ስርዓት ግን ይወገድ።

No comments:

Post a Comment

የምጣዱ እያለ የእንቅቡን፤ የእርስ በርስ ግጭት እና የመንግስት ምላሽ

በያሬድ ሃይለማሪያም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አሁንም ግጭቶች መበራከታቸው እና መፈናቀል መቀጠሉ የአገራችንን ፖለቲካ አሳሳቢ እያደረገው እና አገሪቱንም ወደ ችግር ውስጥ እየከተታት ይመስላል። መንግስት ለችግሮቹ የሚሰ...