Tuesday, April 21, 2015

መንግሥቴ ሆይ ማን ቢሉህ ማንን ታውቃለህ


በሊቢያ የተከሰተውን ዘግናኝ ፣ አናዳጅ ፣ አሳዛኝ ፣ አበሳጭ ፣ አቃጣይ ፣ አስለቃሽ ፣ ጥርስ አስነካሽ ፣ አብከንካኝ ፣ እና ባለ ብዙ ስሜት ባለቤት ኢ-ሰዋዊ ወይም ኢ-ሰብአዊ ግድያ ተከትሎ ፣ ጸሓዩ መንግስታችን አንድ ሁለት ጥያቄዎችን እንዳቀረበ ሰማሁ ።

1) ኢትዮጵያዊ መሆናቸው ይጣራለት ዘንድ
2) የተለቀቀው የድህረ ገጽ የምስል አሸንዳ ( ) እውነተኝነት ተጣርቶ ይቀርብለት ዘንድም


የኛ ጥያቄ መንግስታችን ሆይ ማን ቢሉህ ማንን ታውቃለህ ? እነ ባልቻን ታውቃቸዋለህ ወይ ? እነ እያሱ ትንሽ ትንሽም ቢሆን ትዝ ይሉሃል ወይ ? እነ ዔፍሬም ፣ እነ ዓለም ፣ እነ አከሌ ፣ እነ አከሌን ታውቃቸዋለህ ወይ ?
የኛ ጥያቄ ኢትዮጵያውያኖች ሆነን ብንገኝ ፋይዳ ያለው ነገር ታደርጋለህ ወይ ? ወይስ ይቺን አጋጣሚ ተጠቅመህ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ከ አይሲስ ጋ አቆራኝተህ ፣ ውሻ በቀደደው እንዲሉ ጥናታዊ ፊልም ሰርተህ ታቀርብልን ይሆን ?
እርግጥ ነው እንደ አንተ አይነት በውሸት መረጃና ማስረጃ ዜጎቹን እየከሰሰ ማሰር ፣ መግደል ፣ ማዋረድ ለለመደ፣ ዱርዬ እና ዱር አደር ስርዓት ፣ የሚያዩትን ሁሉ አለማመን ፣ ዓለም የመሰከረውን ፣ ኢትዮጵያዊው ደማችን ታርዶ የተናገረውን ፣ ጥቁር ቆዳችን በርሃ ላይ በባዶ እግሩ ተገፍቶ ፣ አንገቱን ወደ መሬት ቀብሮ ተስፋ ከቆረጡ አይኖች በሚወረወሩ ቃላቶች አሸዋ ላይ የጻፈውን ፣ ይቺ ቀን ታልፍ ዘንድ በጭንቀት አምላኩን በልቡ ሲለምን የሚያስይ ፣ በተንቀሳቃሽ ምስል አሸነዳ የቀረበ ማስረጃ ይረጋገጥ ማለትህ ፣ የዓለም የዜና አውታሮች ስለኛ ማንነት ያመኑትን አለማመንህ ፣ የገባህበትን የውሸት ማጥ ፣ የኖርክበትን የሐሰት ሕይወት ፣ ለኢትዮጵያዊነት ያለህን ንቀት ፣ ለሕዝቦቿ ያለህን መራር ጥላቻ ማሳያ ነው ።

ቆይ ግን ማን ቢሉህ ማንን ታውቃለህ ? እነ ባልቻ እኮ በምርጫ 97 አንተን መራሩን ስርዓት ተቃውመው ሰልፍ የወጡ ልጆች ነበሩ ፣ ያልፈለጉህ ፣ ካንተ ጋ ምንም አንዳች የሚያመሳስል ነገር ያልነበራቸው ፣ በደልህ የሰለቻቸው ፣ ፍትህ የናፈቃቸው ፣ የወጣትነት ጉልበታቸውን ፣ ዘረኛ ስርዓት ሽባ ያደረገባቸው ፣ ሃገራዊ ፍቅራቸውን ፣ ጉልበተኛ መንግስት የነጠቃቸው ። እነ ባልቻ ለምን እንደታረዱ ታውቅ ይሆን ? አዎ በሀገራቸው ሰብአዊ ክብራቸው ሲገሰስ ፣ የመኖር ሕልውናቸው ጥያቄ ውስጥ ሲወድቅ ፣ ጉርሻ የሚሸጥበት ፣ ልጃ-ገረዶች ጭናቸውን አጥበው ለወሲብ እርድ የሚቀርቡባት ፣ ህጻናት ለባእዳን በጉዲፈቻ የሚሰጡባት ፣ ግብረ ሶዶማዊነት ገሃድ የወጣ እውነት የሆነበት ሀገር ኗሪ ልጆች በመሆናቸው ፣ ነገሩ ሁሉ ህሊናቸውን ቢያመው ፣ የነብሳቸውን ቅኔ ሰም ቢያደርገው ፣ ይበሉት ቢያጡ ፣ የሚቆጡት ስርዓት ፣ የሚያኮርፉበት አባት ፣ የሚመኩበት ወገን ቢያጡ ፣ ይሄን ቢያጡ ነው ከሀገር የወጡት ። እንደ ሰይጣን ግብር ንጹህ ደማቸው ባህር ላይ የፈሰሰው ለምን ይመስልሃል ? በየመን እቶን እሳት መጋፊያ የሆኑት ለምን ይመስልሃል ፣ በሳውዝ አፍሪካ ገላቸው መጥረቢያ እስክያደንዝ የተቆራረጡት ለምን ይመስልሃል ፣ እንደ እንኩሮ በእሳት የተቆሉት ለምን ይመስልሃል ፣ የባህር ውሃ በየ ቀኑ የሚበላቸው ለምን ይመስልሃል ? ስላደግን ? ስለተመነደግን ? ቀለበት መነገድ ስለሰራን ? ችግን ስላፈላን ? ይልቅ መንገድ የገነባው መናገር የማይፈቅድ ስርዓት ፣ ባቡር እና ግድብ የሰራው ፣ ዜጎች በእኩልነት መኖር የማይችሉበት መንግስት ፣ ይሄ አደገች ፣ እዚህ ደረሰች ፣ ይህንን ሆነች እያልክ የምታወራላት ሀገር ፣ ከልመና እና ከምጽዋት ሳትወጣ ፣ ልጆቿን በቀን አንዴ እንኳ መመገብ ቢያቅታት ፣ ነው እነ ባልቻ የታረዱት ፣ ደማቸው ደመ ከልብ ሆኖ የቀረው ለምን ይመስልሃል ?

አዎ ማን ቢሉህ ማንን ታውቃለህ ? ይልቅ እንደለመድከው ሆድ አደር ከያኒያን ሰብስበህ ፣ በየ ታንኩ ላይ ተንጠልጥለው ፎቶ ሲነሱ የሚያሳይ ምስል ልቀቅና ይህን ደራሽ ያጣ ሕዝብ አስፈራራበት ። ያንተ ታንክ ፣ መትረየስ ፣ የጦር ጀት የገዛ ህዝብህን ለማስፈራራት እንጂ ፣ ወገኖች
ሲዋረዱ ና ሲታረዱ ፣ የታንክህ ድምጽ ፣ የጦር ጀትህ አፍንጫ የሊቢያ ሰማዮችን ሰንጥቆ እንደማያልፍ እናውቃለን ። ስለዚህ እነማን ናቸው ? ምንድን ናቸው ፣ ይጣራ ፣ ወዘተ ወዘተ አትበለን ። ማን ቢሉህ ማንን ታውቃለህ ! እንኳን የገደልከውን ፣ ያስራብከውን ፣ ባንተ ምሬት ከሀገር እንዲወጣ ያደረከውን ፣ በየ እስር ቤቱ ያጎርከውን ፣ የራስህንም ኢትዮጵያዊነት አታውቅም ! ዝም በል !

ዝም በል አንተ ጭንጋፍ ዘረኛ
ተወን አንተ መርዘኛ ዳተኛ
የኛ ማንነት ፣ አይጣራም ባንተ እውነት
የኛ ደም የፈሰሰው
ዛሬም ነገም ባንተ ነው !
ዝለዚህ ዝም በል !
ቢያንስ ሞታችንን መነገጃ አታድርገው
ተው !
አንተ ርካሽ ጥንብ አንሳ
አንተ የሰይጣን ጎረምሳ
ዝም በል ተወን
እንሙት
ዝም በል ፣ አንተ ዲያብሎስ
አናቴ ከይሲ አንተ እርኩስ
አንተ ጊንጥ መርዛም ተናካሽ
ዝም በል ፣ ሽሽሽ !
ዝም በል ፣ ዝም በል ፣ ዝም በል !

ወይ ነዶ !

ሄኖክ የሺጥላ 

No comments:

Post a Comment

የምጣዱ እያለ የእንቅቡን፤ የእርስ በርስ ግጭት እና የመንግስት ምላሽ

በያሬድ ሃይለማሪያም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አሁንም ግጭቶች መበራከታቸው እና መፈናቀል መቀጠሉ የአገራችንን ፖለቲካ አሳሳቢ እያደረገው እና አገሪቱንም ወደ ችግር ውስጥ እየከተታት ይመስላል። መንግስት ለችግሮቹ የሚሰ...