ሀሌታው ሀ፤
አቶ ሬድዋን ሁሴን የኢህአዴግን ችግር ከተቃዋሚዎች በተሻለ ራሱ ኢህአዴግ ያውቀዋል። መፍትሄውም ያለው እኛው ዘንድ ነው... አሉ።
አሃ... ለካስ ችግሯን አውቃችሁ ፈጥራችሁ መፍትሄዋንም ደብቃችሁ ነው የምታስለፈልፉን... ወይ ጣጣችን ኧረ እኛ ምርጫው ይቅርብን እና ችግሩን አርቁልን! ነውር አይደለም እንዴ... እያወቁ ችግር ፈጥሮ ምርጫ ሲቃረብ ⶭግሩን እናውቀዋለን መፍትሄውንም ይዘነዋል... ማለት!
(ኧረ ረስቼው ስለ መድበለ ፓርቲ ሲወራ አቶ ሬዲ... ምን አሉ... እናንተ አሸባሪዎችን ጀግና እያላችሁ እዚህ ከኛ ጎን መቀመጣችሁ ራሱ ትልቅ የመድበለ ፓርቲ ማሳያ ነው... እንደ ስራችሁ ቢሆን እስር ቤት መውረድ ነበረባችሁ ሲሉ ተናገሩ። የሚያስቅ ነው እነ ሰማያዊ እና መድረክ አሸባሪን ጀግና አላችሁ የሚባሉት እነ አንዷለም አራጌን እና እነ በቀለ ገርባን ጀግና በማለታቸው ነው። ኢህአዴግዬ ራሷ ደጋግማ ያለቸው ነገር ሁሉ ለራሷ እውነት መስሎ እየታያት እንጂ ንጹሃንን ያሰረችው እና የነደፈችው እርሷ ንቧ ፓርቲ ነበረች። እና ፍትህ ቢኖር ኖሮ አቶ ሬድዋን ብቻ ሳይሆኑ ፓርቲያቸው ራሷ በርካቶችን አላግባብ በማሰቃየት ወንጀል እስር ቤት መውረድ ነበረባቸው
ለ፤
የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ሊቀመንበር አሪፍ ኮመዲያን ናቸው... እኒህ ሰውዬ በምርጫ ስልጣን መጨበጥ ቢያቅታቸው በምርጫ ክርክር ያላቸውን ደቂቃ አብቃቅተው ባለስልጣኖችን እና ተቃዋሚዎችን መጨበጣቸው ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። ብለን እኛም በኩምክና እንብለጣቸው እንዴ... በነገራችን ላይ እኒሁ ሰውዬ ባለፈው ምርጫ ወቀት የምርጫ ምልክታቸው አይን ነበር እና በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ በለው.... ''እንግዲህ እየተጠቃቀሳችሁ እኛን ምረጡ'' ብለው በሳቅ ሲያነፍሩን ነበር።
ሐመሩ ሐ፤
አቶ ትግስቱ አወሉ ኢህአዴግ አምባገነን ነው! አሳሪ ነው...! እያሉ ሲቀውጡት የምር እንዴት ድንገጥ አልኩ መሰላችሁ። ትንሽዬ ልጅ አባቱን ሽቅብ ሲሳደብ የሰማሁ አይነት ነው የተሰማኝ! (በቅንፍ ፤ እነ አቶ ሬድዋን ግን አቶ ትግስቱን እንዲያ በራዲዮ ፋና እና ኢቲቪ አስሬ እያነሳሱ ሲያቀብጧቸው እንዳልኖሩ አሁን በዝች ወሳኝ ሰዓት አንድ ጊዜ እንኳ ስማቸውን በክፉም በደጉም ሳይጠሩ መድረክ እና ሰማያዊን አስር ጊዜ ሲያነሱ የምር ታዘብኳቸው)
መ፤
መድረክ እና ሰማያዊ...ስድስት ደቂቃ አነሰችን ስትሉ እንዳልሰማችሁ... ኢህአዴግ ከተሰጠው ሃያ ደቂቃ አስራ ስድስቱ ስለናንተ አይደል እንዴ ያወራላችሁ... (የምር ግን ኢህአዲግ ያልገባው ነገር እርሱ የሚወቅሳቸውን ፓርቲዎች ህዝቡ ቤቱ ቁጭ ብሎ አሃ.... ''እነዚህ ፓርቲዎች ደህና ናቸው ማለት ነው!'' ብሎ እንደሚያስብ ነው) ለማንኛውም የምርጫ ክርክሩ ዛሬም ይቀጥላል። ለኢህአዴግ ሃያ ደቂቃ ሲሰጥ ለመድረክ እና ለሰማያዊ ስድስት ስድስት ደቂቃ መሰጠቱ ግን በጣም አስቂኙ ነገር ነው።
ሀገራችሁን በስድስት መስመር ግጥም ገለጹ የተባለው ተማሪ ትዝ አለኝ፤
''እንኳን ስድስት መስመር መቶም አይበቃሽ
እንደው በደፈናው የጉድ ሀገር ነሽ
አቤ ቶኪቻው
No comments:
Post a Comment