Saturday, December 13, 2014

‪#‎Ethiopia‬ የኢፌዴሪ የት/ሚ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የኢሕአዴግ የምርጫ ድል ልማት ሰራዊት ግንባታ አደረጃጀት ማንዋል፡፡ ለምርጫ 2007

-------------------------------------------------------------------------------------------------------
ይህ ከላይ በርዕሱ የተጠቀሰውና በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተሰራጨው መመሪያ የከፍተኛ ት/ት ተቋም ተማሪዎች በተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰልፍ በማንዋሉ አጠራር “ጠላቶች” ጋር እንዳያብሩ እና ሊከሰት የሚችለውን የተማሪዎች እንቅስቃሴ እንዴት መገደብ እንደሚቻል ያትታል፡፡
ተማሪዎች ምርጫውን ተከትሎ ሁከት እና ብጥብጥ ይፈጥራሉ ብሎ የተነበየው ሰነድ መጥለፊያ መላዎችን ያስቀምጣል፡፡
ማንዋሉ ዓላማ ብሎ ባስቀመጠው ውስጥ ‹‹የፖለቲካ ሰራዊት ግንባታ በሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ በማቀጣጠልና በማስቀጠል ተቋማዊ ለውጡን እውን በማድረግ የትምህርት ጥራትና አግባብነትን ፤ ምርጫ 2007 ውጤታማ በማድረግ እና የኢህአዴግ አሸናፊነት ለማረጋገጥ ነዉ፡፡›› በማለት ለሚመጻደቅበት ‹‹ፍትሐዊ እና ነጻ ምርጫ›› ዝግጁ አለመሆኑን በማስረጃ ይገልጥልናል፡፡


ለማታገያነት ከታሰቡ እና የተማሪውን አጀንዳ ለማስቀየሪያ ይሆናሉ ተብለው የታሰቡት የትምህርት ጥራት፣ እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የሚባሉ ማስቀየሻ punching bags ናቸው፡፡ እነዚህንም ጉዳዮች በማጎን ተማሪው ዋናውን ጥያቄ እንዲረሳ በእቅድ ደረጃ ተነድፏል፡፡

‹‹ምርጫውን እንደምናሸንፍ ቃል የተገባ ቢሆንም›› ከመመሪያው የተወሰደ (ቃል የገባው ምርጫ ቦርድ ይሁን ማን እንደሆነ ባይገለጽም) ፈተናዎች የሚፈጠሩት በሕዝብ እና በራሱ ታማኝ ባልሆኑት ኃይሎች ማለትም በመንግስት ክንፍ አይቀለበስም ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ በዚህም ቀድሞ መዘጋጀት እንዳለበት በመግለጽ ለዚህም የተማረው የኅብረተሰብ ክፍል ጉዳይ ሊታሰብበት እንደሚገባ ይገልጻል፡፡ የተማረ የጠላው መንግስት በዚህ ጨዋታ እንደቀልድ ያወሩትን 40 ዓመት በስልጣን ለመቆየት ሕልሙ ይሄን ምርጫ እንዴት እንደሚያልፈው ግራ ተጋብቶ ይደናብር ይዟል፡፡
ሌላው በዚህ ሰነድ መንግስት ያካሄደውን የእምነት ትንኮሳ እንደትክክለኛ ተግባር በመቁጠር ይሄን የተቃወሙ ተማሪዎች ከኢሕአዴግ ይልቅ ዕምነታቸውን መምረጣቸውን በንጽጽር ያስቀመጠበት አንቀጽ ኢሕአዴግ የድፍረቱን ጥግ እምነታቸውን በአክራሪነት ስም በማስጣል እንዲሁም የእምነት ተቋም አመራሮችን በመቆጣጠር ለስለላ ተግባር መጠቀም እንዲሁም ከቤተ ዕምነት ማራቅ አንዱ ስትራቴጂ እንደሆነ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡
በዚህ ሰነድ ውስጥ ከታጨቁት ቃላት ውስጥ የምናገኘው ‹‹የልማት ሰራዊት ግንባታ›› የሚሉት ቃላት ለልማቱ የሚጨነቁ ቴክኒካዊ ቃላት ሳይሆኑ ስልጣንን ለማራዘሚያነት የሚያገለግሉ የፖለቲካ ጉዳይ መሆናቸውን እና በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ያሉት ከፍተኛ አመራሮች ትኩረት እንዲሰጡበት ያሳስባል፡፡
በማስመሰያ ማዘናጊያ እና ትዕግስትን በሚፈትኑ አታካች ቃላቶች የተሞላው ይህ ሰነድ በተቃርኖ የተሞላ ነው፤ ይህ ሕገ-መንገስቱን የሚጥስና ከሕዝብ ፍላጎት ውጪ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለማንቀሳቀስ የተዘጋጀው የፖለቲካ ሰነድ እዛው ህገ-መንገስቱን አውቆ ስለማሳወቅና ስለተግባራዊነቱም ይሰብካል፡፡
የሲቪል ሰርቪስ የለውጥ ሰራዊት የሚመራባቸው መርሆዎች በሚል ካስቀመጣቸው ንዑስ ርዕሶች ውስጥ የጋራ መግባባት /Consensus/ በሚል ንዑስ ርዕስ ሥር
‹‹የጋራ መግባባትን የምናሳካው በመጀመሪያ ምርጫው የኢህአዴግ የደጋፊ የድል ሰራዊት ብዛት ነው፡፡ በማለት ለአንባቢዎቹ እቅጩን ይነግራል፡፡››
በተጨማሪም ሁሉም የዩኒቨርስቲ ፕሬዜዳንቶች ውጤታቸው የሚሞላላቸው ለምርጫው በሚያዘጋጁት የደጋፊ ሃይል ይወሰናል፡፡ በማለትም ፕሬዝዳንቶቹ ወንበራቸው በምርጫ ምክንያት ሊያጡት እንደሚችሉም ይጠቁማል፡፡
በሙስና የተተበተቡት የፖለቲካ ሹማምንት የሆኑት የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች ባላየ የሚታለፍላቸው ሙስና ለስልጣን ማስቀጠያነት ተቋማቱን መጠቀም ካልቻሉ በሚያገኙት ውጤት ምክንያት ስልጣናቸውን ሲያጡ መድረሻቸው የሙስና እስር ሊሆን ይችላል፣ ይህም በብዙ ባለስልጣናት እንደምናየው ገዢውን በስልጣን የማቆየት ሥራ በፖለቲካ ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ብቻ ሳይሆን ራስን ለማዳን የሚደረግ ትግል ነው፤ ለዚህም ነው እንደዚህ ያሉ ግምገማዎችን ለማለፍ ሲሉ ለሚያስተዳድሯቸው ተቋማት ለቦንድ ግዢ እና መሰል መዋጮዎች በውይይት ሳይሆን ፕሬዝዳንቶች ወሳኝ የሚሆኑት፡፡
ሕግ የለም እንጂ ሰነዱስ ወያኔ (ኢሕአዴግን) ከጨዋታ የሚስወጣው ነበር፡፡ ይህ ሰነድ ኢሕአዴግ እንዲህ አደረገ ተብሎ እንዲታለፍ አልፈልግም የፖለቲካ ተቋማት፣ ማኅበረ ቅዱሳን፣ ድምጻችን ይሰማ፣ እና ሌሎችም ይህን መረጃ እንደግብአት ተጠቅመው ማርከሻውን ያዘጋጁ ዘንድ የሚንቀሳቀሱ ከሆነ መረጃውን ለማጋራት ዝግጁ ነኝ፡፡
(በውስጥ መስመር ይጠይቁ)

No comments:

Post a Comment

የምጣዱ እያለ የእንቅቡን፤ የእርስ በርስ ግጭት እና የመንግስት ምላሽ

በያሬድ ሃይለማሪያም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አሁንም ግጭቶች መበራከታቸው እና መፈናቀል መቀጠሉ የአገራችንን ፖለቲካ አሳሳቢ እያደረገው እና አገሪቱንም ወደ ችግር ውስጥ እየከተታት ይመስላል። መንግስት ለችግሮቹ የሚሰ...