Wednesday, November 5, 2014

ሴት ጦማሪያን ፍርድ ቤት የሰጠላቸውን ትዕዛዝ ማረሚያ ቤት አላከበረም አሉ



-መዝገቡን መርምሮ ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ

በተጠረጠሩበት የሽብርተኝነት ወንጀል በእስር ላይ የሚገኙት ሴት ጦማሪያን፣ የመብት ጥሰት እየደረሰባቸው መሆኑን በመግለጽ ለፍርድ ቤት አመልክተው ፍርድ ቤቱ እርማት እንዲወስድ የሰጠውን ትዕዛዝ፣ የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ተግባራዊ አለማድረጉን ጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ለፍርድ ቤት አመለከቱ፡፡


ተጠርጣሪዎቹ ጦማሪያን ማህሌት ፋንታሁንና ኤዶም ካሣዬ፣ በማረሚያ ቤት እየደረሰባቸው የሚገኘውን መገለልና በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን ንፁህ ሆኖ የመገመት መብታቸውን እያጡ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ቀደም ብሎ በሰጠው ትዕዛዝ፣ ጦማሪያኑ እንደ ማንኛውም ተጠርጣሪ፣ ተጠርጣሪ መሆናቸውን ገልጾ፣ ከማንኛውም ታራሚ እኩል እንዲታዩ ትዕዛዝ መስጠቱን አስታውሰዋል፡፡ በተጨማሪም ቤተሰቦቻቸው ‹‹ለአሥር ደቂቃ ብቻ›› እንደሚጠይቋቸው በመግለጽ አንስተውት ለነበረው አቤቱታም፣ ፍርድ ቤቱ እንዲስተካከል ተናግሮ፣ ይኸ ሳይሆን ቀርቶ ተጠርጣሪዎቹ በድጋሚ አቤቱታ የሚያቀርቡ ከሆነ፣ ምርመራ አድርጐና አጣርቶ ተገቢ ዕርምጃ እንደሚወስድ ጥብቅ ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም፣ ተግባራዊ እንዳልተደረገላቸው በድጋሚ በአቤቱታቸው አስረድተዋል፡፡

ቤተሰቦቻቸው ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ትዕዛዝ በመስማታቸው፣ እንደ ማንኛውም ጠያቂ ከጠዋቱ አራት ሰዓት በማረሚያ ቤት የተገኙ ቢሆንም፣ እንዲገቡ የተፈቀደላቸው እንደተለመደው በስድስት ሰዓት ሆኖ ለአሥር ደቂቃ ብቻ መሆኑንም አክለዋል፡፡ ያስመዘገቧቸው ወላጆች አዛውንቶች በመሆናቸው፣ ማረሚያ ቤት ድረስ በየቀኑ ተመላልሰው መጠየቅ እንደማይችሉ በመግለጽ፣ እንደ ማንኛውም ተጠርጣሪ ሌሎች ዘመዶቻቸው እንዲጠይቋቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው አመልክተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የማረሚያ ቤት ተወካይን ሲጠይቃቸው፣ ቀደም ባለው ችሎት የማረሚያ ቤቱ ሴት ታራሚዎች ክፍል ኃላፊ ቀርበው ሁሉም ነገር እንደ ማንኛውም ተጠርጣሪ እየተደረገላቸው ነው፤›› ብለው ማስረዳታቸውን በማስታወስ፣ አሁንም ፍርድ ቤቱ የሚሰጠውን ትዕዛዝ ከማድረስ ባለፈ የሚሉት ነገር እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ጦማሪያኑ እየደረሰባቸው ያለውን ‹‹አሸባሪዎች ናቸው›› በሚል መገለላቸውንና ሌሎች በደሎችንም በጽሑፍ ባቀረቡት አቤቱታ ተቀብሎ፣ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በቀጣይ ቀጠሮ የማረሚያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ቀርበው እንዲያስረዱ አዟል፡፡ ፍርድ ቤቱ በዕለቱ ቀጠሮ ይዞ የነበረው፣ ዓቃቤ ሕግ በመሠረተው ክስ ላይ ጦማሪያኑ ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያና ዓቃቤ ሕግ በድጋሚ በክስ መቃወሚያው ላይ የሰጠውን ምላሽ መርምሮ ብይን ለመስጠት ነበር፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ መዝገቡን መርምሮ አለመጨረሱን በመናገር ብይን ለመስጠት በድጋሚ ተቀጥሯል፡፡

No comments:

Post a Comment

የምጣዱ እያለ የእንቅቡን፤ የእርስ በርስ ግጭት እና የመንግስት ምላሽ

በያሬድ ሃይለማሪያም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አሁንም ግጭቶች መበራከታቸው እና መፈናቀል መቀጠሉ የአገራችንን ፖለቲካ አሳሳቢ እያደረገው እና አገሪቱንም ወደ ችግር ውስጥ እየከተታት ይመስላል። መንግስት ለችግሮቹ የሚሰ...