አዎ፣ ይመለስ!! ፍርሃቱን ጭቆናን የማሸነፊያ ብቸኛ መንገድ የፍርሃት ሰንሰለትን ሰባብሮ፣ በእምቢተኝነት ደም-አልባ ሰላማዊ አመፅ የገዥዎችን ሰፈር ማራድ፤ እኩይ አላማዎቻቸውን የሚያስፈፅሙ ተቋማትን ጥርስ አልባ ማድረግ፤ አደባባዮችን በሰው ጎርፍ ማጥለቅለቅ፤ የትኛውንም አይነት ተቋማዊ ትብብርን መንፈግ፤ ኤፈርትና መሰሎቹን የንግድ ድርጅቶቻቸውን ማግለል፤ ሁሉም ፖለቲካዊ ፍላጎቶቻችን በኢትዮጵያዊ ዜግነት ስር እንደሚፈቱ ከልብ በማመን-ነገን ማለም፤ ለጥያቄው እስኪንበረከኩ ድረስ በሰላማዊው ተቃውሞ ፀንቶ መቆምንና መሰል ስልቶችን መተግበር ብቸኛ አማራጭ ነው፡፡ ይህ ይፈፀም ዘንድም የተሸሸገ ፍርሃትን የተሻገሩ ጎበዛዝትና ወይዛዝርት ሊፈተኑበት፤ ከሽፈው የቀሩት ደግሞ ጥያቄውን በማጥላላትም ሆነ የተራራ ያህል በማግዘፍ ፍርሃትን አንብረው የአገዛዙን ዕድሜ ለማራዘም ደፋ-ቀና ከማለት ይታቀቡ ዘንድ የሚገደዱበት ዕለት ከደጅ መድረሱን ለመተንበይ ነብይ መሆንን አይጠይቅም፤ አይኖች-ያያሉ፤ ጆሮዎችም- ይሰማሉና፡፡
የተጠናወተህን ገደብ አልባ ፍርሃት፣ ለውጥ የሚጠይቁ ድምፆችን በማጣጣል ለመሸፋፈን መዳከር የት ያደርስሀል? የወላዋይ ብዕርህን ‹‹የለሁበትም!!›› ቅኔ ለበስ አቤቱታ እና ‹እውነት ለመናገር ጊዜና ቦታ አለው› የሚል ፍርሃታዊ ማምለጫህንስ ስለምን ለታናናሾችህ ለመጋት ትደክማለህ? በአገዛዙ መዝገበ-ቃላት ‹‹ፅንፈኛ፣ ጀብደኛ…›› ብለህ ማምታታትስ ባለፈ ዘመን ላይ መከተር አይደለምን? እውነት እውነት እልሀለሁም፡- በሰላማዊ መንገድ የስርዓት ለውጥን መጠየቅ፣ በ‹አትነሳም ወይ!› የሀገር ባለቤትነት ከፍታ ለአደባባይ ተቃውሞ ዘመነኞችን በእሪታ መጣራት፣ በየትኛውም የታሪክ ስፍር ጀብደኝነት ሆኖ አያውቅም፤ ለሕሊና መታመን እንጂ፡፡
ለነገሩ ቢዘገይም ታሪክ ከእውነት እንጂ ከፍርሃት ውል ኖሯት አያውቅም፡፡
የዐድዋ ገድል፣ እልፍ አእላፍ የሀገሬ ሰዎች መተኪያ አልባ ህይወታቸውን የገበሩበት በመሆኑ፣ በየዓመቱ ደግመን ደጋግመን የመዘከርና አደራውን የመቀበል ታሪካዊ ግዴታ ውስጥ ጥሎን ማለፉ እውነት ነው፡፡ ‹‹የተሰጠኝ ህይወት ዛሬ በነፃነት፣ ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት›› እንድትል እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ)
Hana Boru
No comments:
Post a Comment